ሚኒስቴሩ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል 361 ሺሕ 415 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ገለጸ

ሐምሌ 4/2015 (ዋልታ) በኢትዮጰያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ለተያዘው እቅድ 361 ሺሕ 415 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የተፈጠሮ ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) በአንድ ጀንበር ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር 9 ሺሕ 500 የመትከያ አካባቢዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።

ለ500 ሚሊየን ችግኞች መትከያ 361 ሺሕ 415 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴታው በዕለቱ በየአካባቢው የሚደረጉ የችግኝ ተከላዎችን ከስፍራው በቀጥታ ለዓለም ህዝብ ተደራሽ ለማድረግ የካርታና GREENLEGACY.ET የዌብ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር 9 ሺሕ 500 ቦታዎችን በካርታ የማካተትና ድረገፅ በማበልፀግ ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።

በእለቱ ከ25 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በችግኝ ተከላው እንደሚሳተፍ ጠቅሰው ዜጎች ሁሉ በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን እንዲያኖሩ ሚኒስትር ዴታው ጥሪ ማቅረባቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

#በአንድ_ጀምበር_500_ሚሊየን_ችግኝ
#ነገን_ዛሬ_እንትከል
#ዐሻራ_ለትውልድ
#ይህ_የኢትዮጵያ_ጉዳይ_ነው!