ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተከፈተውን መጠነ ሰፊ የጥላቻ ዘመቻ በጋራ ልናወግዝ ይገባል

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ እንዳመላከተው የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ዳር ድንበር በመጠበቅ ውድ ህይወቱን እየገበረ እንደ ሀገር እንድንቀጥል አድርጎናል።

በአንድ በኩል ከውጭ የሚሰነዘርን ጥቃት በአስተማማኝ ደረጃ በመመከት ሉአላዊነታችንን ያስጠበቀ እና የእኛነታችን መገለጫ የሆነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ህገ መንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በመጠበቅ የሰላም አየር እንድንተነፍስ እያደረገ ይገኛል።

ሰራዊቱ ከራሱ ይልቅ ለሀገር እና ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ እና መልከአምድር እየተንገላታ ላፍታም እረፍት ሳያገኝ ሌት ተቀን እየተጋ መሆኑን ሁሉም የሚገነዘበው ሀቅ ነው።

የሀገሪቱ ደጀን በመሆን የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ስም ማጠልሸት እና ክብሩን በማይመጥን ሁኔታ እየተካሔደ ያለውን መጠነ ሰፊ የጥላቻ ዘመቻ በጋራ ልናወግዝ ይገባል።

ሰራዊቱን መንካት ማለት የሀገርን ሉዓላዊነት እንደመዳፈር የሚቆጠር በመሆኑ የክልሉ ህዝብ እና መንግስት ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆኑን እናረጋግጣለን።

የክልሉ ሕዝብ መብቶችና ጥቅሞች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጥቅሞች ጋር የተያያዙ እንደመሆናቸው ሀገራዊ አንድነታችንን በማጽናት ጥንት አባቶቻችን በደም እና በአጥንት ያቆዩልንን ሀገር ለተተኪው ትውልጅ ማቆየት ይጠበቅብናል።

የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ በመመካከር መፍትሄ መሻት የስልጣኔ መገለጫ ነው ።እናም የትጥቅ ትግልን ዋነኛ አማራጭ በማድረግ የሚመለስ ጥያቄ አለመኖሩን ልብ ሊባል ይገባል።

በክልሉ የጠመንጃ አፈሙዝን አማራጭ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ኃይል የክልሉን ሕዝብ ስቃይ እጥፍ ለማድረግ የተፈጠረ እንጂ የአማራ ክልል ህዝብ ወኪል ሊሆን አይችልም።

በገዛ በወገኖቹ ላይ የጭካኔ ተግባር እየፈጸመ ያለውን ሀገር አፍራሽ ኃይል ለመታገል በሚካሔደው ጥረት የክልሉ መንግስት ከአማራ ክልል ጎን እንደሚሆን ማረጋገጥ እንወዳለን።

የአማራ ክልል ህዝብ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት ብዙ መከራና ስቃይ አሳልፏል።ከደረሰበት መከራ ሳያገግም ዳግም ችግር ውስጥ እንዲገባ በመደረጉ የክልሉ መንግስት በእጅጉ አዝኗል።

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ነሐሴ 1/2015
ሀዋሳ