ደቡቡን የሀገራችን ክፍል ከምዕራቡ ጋር የሚያገናኘው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አስፋልት የማንጠፍ ስራ ተጀመረ


ነሐሴ 1/2015 (አዲስ ዋልታ) ደቡቡን የሀገራችን ክፍል ከምዕራቡ ጋር በሚያገናኘው የሳላይሽ-ኦሞ ኮንትራት-3 የ37 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አስፋልት የማንጠፍ ስራ ተጀመረ፡፡

የሁለት ኪሎሜትር የአስፋልት ንጣፍ ስራ የተከናወነ ሲሆን የጠረጋ፣ የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት፣ የሰብቤዝ እና ቤዝኮርስ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ እንዲሁም የሦስት ድልድዮች ግንባታ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑ ተጠቅሷል።

የግንባታውን አጠቃላይ ሥራ በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ሲሆን ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቱ በሌላ ሀገር በቀል የሥራ ተቋራጭ ድርጅት ሲከናወን የቆየ ቢሆንም ከአፈጻጸም ውስንነቶች ጋር በተያያዘ ሲጓተት መቆየቱ ተጠቁሟል።

የመንገድ ስራውን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ508 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የግንባታውን ቀሪ ሥራ ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሠራ እንደሚገኝም ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የመንገዱ ግንባታ ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለው የተጠቆመ ሲሆን በዋናነትም የኦሞ-ወንዝ የሚያቋርጥበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በስፋት የግብርና እንዲሁም የስኳር ፋብሪካ ምርት ውጤቶችን ወደ ተለያዪ የሀገሪቷ ክፍሎች ለማድረስ እንደ አማራጭ ያገለግላል ተብሏል፡፡

ከዚህ ባሻገርም የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪስቶች ምቹ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።