ከድሬዳዋ አስተዳደር ወቅታዊ ጉዳይን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ድንቅ እሴቶች መካከል በህዝቦቿ ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አለመግባባት የሚፈቱበት የተለያዩ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ባለቤት መሆኗ ከሰማኒያ በላይ ብሔሮች ብሔረሰቦች ለዘመናት ነፃነቷን እና ሉዓላዊነቷን አስጠብቀው በአንድ ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ሥር የኖሩባት ሀገር ነች፡፡ በቅርብ ታሪካችንም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊነት መገለጫ በሆነው ህገ-መንግሥት የሚነሱ አለመግባባቶችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች በግልጽ ተደንግገው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በሥራ ላይ ውሎ ይገኛል፡፡

ይሁንና ግን ያሉንን በርካታ አማራጮችን ወደጎን በመተው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በኢ-መደበኛ አደረጃጀት የታጠቁ ኃይሎች ከብሔሮች ብሔረሰቦች የተገነባ የሀገር የመጨረሻ ምሽግ፣ የአንድነታችን አርማ፣ የሀገር እና ዜጎች አለኝታ እና የቁርጥ ቀን የህዝቦች መከታ በሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመተንኮስ የጀመሩት ጦርነት መከላከያን መንካት የሀገርን ሉዓላዊነት መዳፈር በመሆኑ እንዲሁም ክልሉ ከጦርነት ጉዳት ሳይወጣ ይሄ ችግር ስለደረሰበት አስተዳደራችንን በጣም አሳዝኖታል፡፡

ስለሆነም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው አለመግባባት የደረሰብንን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በቅጡ ሳናገግም ይህ በክልሉ የተቀሰቀሰው ጦርነት የሰው ልጅ ከተጎዳ እና በንብረት ላይ አስከፊ ጉዳት ካደረሰ በኃላ የውይይት አማራጭ ከማፈላለግ አስቀድሞ ነፍጥ ያነሱ ሁሉ በክልሉ እና ፌዴራል መንግሥት የቀረበላቸውን ሁነኛ የሠላም አማራጭ ተቀብለው የሀሳብ ልዩነቶችን ሁሉም አሸናፊ በሚሆንበት ሠላማዊ ድርድር መቋጭት እንደሚገባ አስተዳደራችን በእጅጉ ያምናል፡፡

በአስተዳደራችንም ይህን አለመግባበት ተከትሎ ከህውከት እና ትርምስ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር እዚህም እዚያ የሚታትሩትን ፀረ-ሠላም ኃይሎች በአስተዳደሩ ሠላምና በህዝብ ደህንነት ላይ ችግር ሊፈጥሩ ስለሚችሉ የተለየ እና ያልተፈቀደ ተግባር ሲያጋጥም እንደቀድሞው ሁሉ የህግ የበላይነት እንዲሚረጋግጥ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የበኩላችሁን ሀገራዊ ኃላፊነት እንድትወጡ አስተዳደሩ ጥሪ ያቀርባል፡፡

ይህ በክልሉ የታጠቁ ኃይሎች የቀሰቀሱት ጦርነት ከክልል በዘለለ ለሀገር ሠላም እና ደህንነት ስጋት ከመሆኑ አስቀድሞ በአሁኗ ኢትዮጵያ ሁኔታ በትጥቅ ትግል የሚመለስ አንዳችም ጥያቄ አለመኖሩን እንዲሁም ጃውሳው የአማራ ክልል ህዝብን ለማሰቃየት የተፈጠረ ኃይል እንጂ የአማራ ክልል ወኪል አለመሆኑን በመገንዘብ የተፈጠረውን አለመግባባት በሠላማዊ ሁኔታ እንዲፈታ ከክልሉ ህዝብ ጋር ይህን አፍራሽ ተልዕኮ ያነገበ ኃይል አስተዳደራችን እንደሚታገል ያለውን ቁርጠኝነት ይገልጻል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር
ነሀሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም
ድሬዳዋ