የአገሪቱን ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ዶክተር ሊያ ታደሰ

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ

ነሐሴ 7/2015 (አዲስ ዋልታ) የአገሪቱን ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ሚኒስትሯ በአዲስ አበባ የሚገነባውን የባዮ ባንክና የላቦራቶሪ የጥራት ማረጋገጫ ናሙናዎች ማምረቻ ማዕከል ግንባታን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ማዕከሉ የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት የላቦራቶሪ የጥራት ደረጃ ፍተሻዎችን በአገር ውስጥ እንዲያገኙ ያስችላል።

የበሽታዎች ቅኝት በማድረግ በወረርሽኝ መልክ ለሚከሰቱ የጤና አደጋዎች ተገቢውን ምላሽ ለመሥጠት ላቦራቶሪው የሚሰጣቸው መረጃዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን የጥራት ናሙናዎች ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በግዥ እንደሚገኝ ገልጸው ይህም የላቦራቶሪ አገልግሎቱ ሥርዓቱ የተሟላ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ሲዳርግ መቆየቱን በማንሳት።

 

በመሆኑም ዛሬ ግንባታው የተጀመረው ማዕከል ወደ ሥራ ሲገባ እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ የአገሪቱን የላቦራቶሪ አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው የማዕከሉ ግንባታ በሽታ አምጭ ተህዋሲያንን የያዙ ናሙናዎችንና መረጃዎችን በጥንቃቄ ለማስተዳደር የሚያስችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ

ይህ ፕሮጀክትና ሌሎች በግንባታ ላይ ያሉ መሰል ግንባታዎች ሲጠናቀቁ የአገሪቱን የጤና ሥርዓት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽሉ ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የማዕከሉ ግንባታ በ885 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚከናወን ሲሆን ወጪው በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ ይሸፈናል ተብሏል።

ማዕከሉ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገነባ ሲሆን 3 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያርፋልም ነው የተባለው።

በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ማዕከል በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆንም ተጠቁሟል።