ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)

ነሐሴ 15/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግቱን አስታወቀ፡፡

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) በበጀት ዓመቱ 400 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት መቻሉንም በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ተቋሙ የ97 ነጥብ 59 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረው የዋጋ ንረትና አለመረጋጋት፣ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ የኮንቲነር አቅርቦት እጥረት እንዲሁም በሀገሪቱ የነበሩት አለመረጋጋቶች በተለይም የጨረታና ግዢ አሰራር ኋላ ቀር መሆን ትልቅ ተግዳሮት እንዳሳደሩበትም ተገልጿል፡፡

በ2015 በተቋሙ የተስተዋለውን ክፍተት በ2016 ለማስተካከል በስልጠና የታገዘ አሰራርን በመዘርጋት እና ዘመናዊ ወደብና ተርሚናልን በማስተሳሰር በዲጂታል የታገዘ አሰራርን ለመከተል መታቀዱን ዋና ስራ አሰፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት