ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ትብብር ለማጎልበት ትኩረት ሰጥታ ትሰራለች – አምባሳደር እፀገነት በዛብህ

ነሐሴ 17/2015 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ትብብር ለማጠናከር በትኩረት እንደምትሰራ በዩጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር እፀገነት በዛብህ ገለጹ።

ለዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት አምባሳደር እፀገነት ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተላከ የሰላምታና የመልካም ምኞት መልዕክት ለፕሬዝዳንቱ ማቅረባቸውም ተገልጿል።

አምባሳደር እፀገነት ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ያላት ግንኙነት ስትራቴጂካዊ መሆኑን ገልጸው በሁለቱ አገራት መካከል የባህልና የተፈጥሮ ተመሳሳይነት መኖሩን አንስተዋል።

በዩጋንዳ ቆይታቸው አገራቱ ያላቸውን የዳበረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ፣ የሕዝብ ለሕዝብ እንዲሁም የኢኮኖሚ ግንኙነቱን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰሩ ለዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ገልጸውላቸዋል።

የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አገራቱ በሁለትዮሽ፣ በክልላዊ እና ዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች ላይ በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸው ያላቸውን የባህልና የቋንቋ ትስስርም መንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አምባሳደሯም በዩጋንዳ የተሳካ የስራ ቆይታ እንዲኖራቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።