በቀጣይ ሶስት ዓመታት ለዘጠኝ ሚሊዮን ዜጎች አዳዲስ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር ታቅዷል – ፍጹም አሠፋ (ዶ/ር)

ነሐሴ 16/2015 (አዲስ ዋልታ) ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም በሚተገበረው ሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ለዘጠኝ ሚሊዮን ዜጎች አዳዲስ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር መታቀዱን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሠፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

በዕቅድ ዘመኑ በመጀመሪያው ምዕራፍ ዝቅተኛ አፈጻጸም የነበራቸው ዘርፎች የማካካሻ ዕቅድ እንዲያፀድቁ፣ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ደግሞ ተጨማሪ ግብ እንዲኖራቸው ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።

የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ አፈጻጸም እና የሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሠፋ (ዶ/ር) ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ሰው ሰራሸና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች በ10 ዓመት መሪ ዕቅድ አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደራቸውን ጠቅሰዋል።

መልከ ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩም በመጀመሪያው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ አፈጻጸም በበርካታ ዘርፎች ውጤታማ እንደነበር መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለአብነትም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስመንትና በግብርናው ዘርፍ የተገኘው ውጤት ከዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ዐውድ አንጻር ሲገመገምና በ10 ዓመት ዕቅድ ከተመላከተው ግብ አኳያ ሲታይ በተሻለ ደረጃ መፈጸሙን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ችግሮችን ተከትሎ የተከሰተው የዋጋ ንረት ትልቁ ተግዳሮት ቢሆንም በተሰሩ ተከታታይ ስራዎች መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።

በዘርፎች መካከል የአፈጻጸም ልዩነት መስተዋሉን ገልጸው በጥቅሉ ሲታይ ግን የተመዘገበው ውጤት አበረታች ነበር ብለዋል።

የዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት የፋይናንስ አቅርቦት በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው ማህበረሰቡን በማስተባበር የፋይናንስ እጥረቱን በሀገር በቀል አማራጭ ለመተካት ጥረት መደረጉን አንስተዋል።

ለአብነትም ማህበረሰቡን በማስተባበር በቱሪዝም መዳረሻ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የተከናወኑ ተግባራት በኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ላይ የራሳቸው ሚና ነበራቸው ብለዋል።

ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም በሚተገበረው ሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ በመጀመሪያው ምዕራፍ ዝቅተኛ አፈጻጸም የነበራቸው ዘርፎች የማካካሻ ዕቅድ እንዲያቅዱ፣ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ደግሞ ተጨማሪ ግብ እንዲኖራቸው መታቀዱን አንስተዋል።

ከእነዚህም መካከል የግብርናው ዘርፍ ተጨማሪ ግብ የተጣለበት ሲሆን የቱሪዝም፣ ማዕድንና አምራች ዘርፎች ደግሞ የማካካሻ ዕቅድ እንዲኖራቸው መቃቀዱን ጠቅሰዋል።

በዚህም የወርቅ የገበያ ድርሻ ከአራት ቶን ወደ 13 ቶን፣ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የገበያ ድርሻ ወደ 46 በመቶ ለማሳደግ እንደታቀደ ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ በ2016 ምርት ዘመን ብቻ ተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ወደ ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን በማጎልበት በእንስሳት ልማት ዘርፍ ትልቅ ዕመርታ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

በጤና፣ በትምህርት፣ በውሃ፣ በኤሌክትሪክ አገልግሎት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንዲሁም የዋጋ ንረትን መቆጣጠር የቀጣይ ሶስት ዓመታት ትኩረቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።