በጎነት ኢትዮጵያውያንን ፈታኝ ሁኔታዎችን አሻግሮ ዛሬ ላይ ያደረሳቸው እሴት ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ጳጉሜን 3/2015 (አዲስ ዋልታ) በጎነት ለኢትዮጵያውያን የአብሮነታቸው ድልድይ፣ የትስስራቸው ገመድ ሆኖ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን አሻግሮ ዛሬ ላይ ያደረሳቸው ትልቅ እሴት ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጳጉሜን 3 “በጎነት ለሀገር” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከናወነ ያለውን የበጎነት ቀንን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል።

የመልዕክቱ ሙሉ ቃልም እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በጎነት ለሃገር!

በጎነት የአእምሮ እርካታ የምናገኝበት፣ ደስታን የምንፈጥርበት፣ ሃገር የምትለማበት በሰውነታችን የታደልነው ስጦታ ነው፡፡

በጎነት የተትረፈረፈ ሃብት ስላለን ወይም አቅማችን የተለየ ስለሆነ የምንፈፅመው ሳይሆን ሁሉም ሰው የታደለው ፀጋና እምቅ ሃይል ነው፡፡

ፀጋውን ወደ ተግባር ስንቀይር የሌሎች ህይወትን የሚቀይር፣ ችግር ውስጥ ያሉትን እንባ የሚያብስ ስጦታ ነው፡፡

የሌሎች ህይወትን መቀየርና ከችግር መታደግ ደግሞ ትልቁ የአእምሮ እርካታ ምንጭ ነው፡፡

በጎነት ለኢትዮጵያውያን የአብሮነታቸው ድልድይ፣ የትስስራቸው ገመድ ሆኖ ከትናንት እስከ ዛሬ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን አሻግሮ ዛሬ ላይ ያደርሳቸው ትልቅ እሴት ነው፡፡

ካለበጎነት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብዙ ፈታኝ ጊዜን ተሻግረው በጋራ ደምቀው ችግራቸውን አልፈው ባልቀጠሉ ነበር፡፡

ዛሬ የበጎነት ቀንን ስናከብር በሁሉም ዘርፍ ያሉ በጎ አድራጊዎችን የበለጠ ለማክበርና ሌሎች ብዙ በጎ አድራጊዎችን ለመፍጠር ነው፡፡

ኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞን ከጀመረችበት ከባለፉት ጥቂት አመታት ጀምሮ መንግስት ለበጎ ስራዎች በሰጠው ትኩረት የብዙዎች እንባ ታብሷል፣ የፈረሱ ቤቶችን ተጠግነዋል፣ አስታዋሽ ያጡ አቅመ ደካሞች የቤት ባለቤት ሆነዋል፡፡

በመሆኑም በጎነት ከትናንት እስከ ዛሬ ካሻገሩን መልካም እሴቶቻችን መካከል አንዱና ዛሬም አጠናክረን ለቀጣዩ ትውልድ ልናሻግረው የሚገባው እሴታችን ነው፡፡

የበጎ አገልግሎትን ወጣቶች እና ህጻናት በሩቁ የሚሰሙት ሳይሆን የቀን ተቀን የህይወት ልምምዳቸው እንዲሆን መንግስት የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ቀርጾ አበይት ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን በዚህም ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተመዝገበውበታል፡፡

ዛሬም “በጎነት ለራስ ነው” በሚል መርህ እየተገዛን ባለን አቅምና ችሎታ ሁሉ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለሀገራችን እና ለህዝባችን የሚጠበቅብንን ሀላፊነት መወጣት ከቻልን በብዙ መልኩ ከባድ የሚመስሉ ችግሮችን መሻገር እንደምንችል የጥቂት ዓመታት የጥረታችን ውጤቶች ማሳያዎቻችን ናቸዉ፡፡

እንኳን ለጳጉሜ 3 የበጎነት ቀን በሰላም አደረሳችሁ!
በጎነት ለሃገር!

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት