ፌዴራል ፖሊስ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አመራሮችና አባላት እውቅና ሰጠ

መስከረም 05/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተሻለ የስራ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት እውቅና ሰጠ።

“እየተሰዋን ሀገር እናፀናለን! ትውልድ እናሻግራለን” በሚል መሪ ቃል ነው የእውቅና መርሀ ግብሩ የተከናወነው።

በእውቅና መርሀ ግብሩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት፣ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኜ ምህረት ደበበን (ዶ/ር) ጨምሮ የፌድራል ፖሊስ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመረሃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ኢትዮጵያ ህልውናዋ እና ሉዓላዊነቷ አደጋ በተጋረጠበት ጊዜ ሁሉ የፖሊስ ሰራዊቱ ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ጊዜያት በርካታ የሪፎርም ስራዎች ሲከናወኑ መቆየቱንም አንስተዋል።

በተለይ በሰው ሀብት በጤና ዘርፍ በፖሊስ ኢንተለጀንስ በሎጀስቲክስና በሌሎች ቴክኖሎጂን ማዘመን ላይ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኜ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በአህጉር ደረጃ ፖሊስ በርካታ እውቅና እያገኘ መሆኑን ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የምንጠብቃቸው ተቋማት ላይ ምንም አይነት አደጋ እንዳይደርስ በቁርጠኝነት እየሰራን ነው ያሉት ምክትል ኮምሽነሩ በቀጣይም በአንድነት በመቆም ለሀገራችን ሰላም ዘብ መቆም ይጠበቅብናል ብለዋል።

በመርሀ ግብሩ ለክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ለዋና መምሪያ ሀላፊዎች እንደሁም ለአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ምህረት ደበበ (ዶ/ር) ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ምህረት ደበበ (ዶ/ር) የፌድራል ፖሊስ የክብር አምባሳደርነት መታወቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በብሩክታይት አፈሩ