ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘላቂ የልማት ግቦች በሚመክረው ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው

መስከረም 7/2016 (አዲስ ዋልታ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ በኒውዮርክ ከሚካሄደው 78ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ቀደም ብሎ እየተካሄደ ባለው የዘላቂ የልማት ግቦች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡

በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ እየመከረ በሚገኘው በዚህ ጉባዔ የኮቪድ-19 ተፅዕኖ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች ሀገራት የቀረጿቸውን ዘላቂ የልማት ግቦች ባቀዱት የጊዜ ሠሌዳ መሠረት እንዳይተገብሩ ማስተጓጎላቸው ተመላክቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበለጸገች እና ሠላማዊ ዓለምን ዕውን ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል፡፡

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካትም ጊዜ ያለፈባቸውና ኢፍትሃዊ የፋይናንስ ተቋማትና ማዕቀፎች መለወጥ እንደሚገባም ዋና ጸሐፊው ማሳሰባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት አባል አገራት መሪዎች የሚሳተፉበት 78ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በነገው ዕለት እንደሚጀመርም በመረጃው ተጠቁሟል፡፡