የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ 61 በመቶ መድረሱ ተገለፀ

መስከረም 17/2016 (አዲስ ዋልታ) በኦሞ ሸለቆ ተፋሰስ ከሚሰሩ ትላልቅ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ውስጥ አራተኛ የሆነው የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አጠቃላይ ስራው 61 በመቶ መድረሱ ተገለፀ፡፡

ከታላቁ ህዳሴ ከግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ የተነገረው ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 1800ሜጋ ዋት የሚያመነጭ መሆኑ ታውቋል።

ግድቡ 6 ዩኒቲቶች እንደሚኖሩት እና እያንዳንዳቸው 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንደሚኖራቸው የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዓባይነህ ጌትነት ጠቅሰዋል።

የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዓባይነህ ጌትነት

የማመንጫ ቤቱ ግንባታ 52 በመቶ መድረሱም ተጠቅሷል።

ግድቡ 201 ሜትር ቁመት እንደሚኖረው የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዓባይነህ ያብራሩ ሲሆን 200 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሸፍናልም ብለዋል።

አጠቃላይ ወጪው 2.4 ቢሊየን ዩሮ የሆነው ይህ ፕሮጀክት ግንባታው ሲጠናቀቅ 200 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 130 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሰው ሰራሽ ሀይቅ እንደሚኖረውም አውቋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ በበኩላቸው፣ የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ለሥነ-ምኅዳር ተስማሚ መሆኑን ገልጸው፣ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን የቱሪዝም መስህብ እንዲሆኑ አስተሳስሮ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብም ወደፊት የሚኖረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ አካባቢው ካለው የቱሪዝም ፀጋ ጋር ተዳምሮ ለዘርፉ ተጨማሪ መዳረሻ እና መስህብ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

የዊ ቢዩልድ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር ዞፒስ

ግድቡ ዊ ቢዩልድ (በቀድሞ ስሙ ሳሊኒ) ተቋራጭነት እየተሠራ ሲሆን የፕሮጀክቱ ማናጀር ኢንጂነር ዞፒስ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አቅም በግድቦች ግንባታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በማሳያነትም በኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ከጉልበት ሥራ እስከ ከፍተኛ ባለሙያ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በኢትዮጵያዊያን እየተገነባ ነው ብለዋል።

በሳራ ስዩም