በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ፖሊስ እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ


መስከረም 20/2016 (አዲስ ዋልታ) በሀረሪ ክልል የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ፖሊስ እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በቅርቡ ለተመረቁ አዳዲስ የፖሊስ አባላት የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም ፖሊስ ከራሱ በፊት ለህዝብ ቅድሚያ የሚሰጥና አርበኝነትን የሚጠይቅ ሙያ ነው ብለዋል።

አዳዲስ የፖሊስ አባላቱም የክልሉን የፖሊስ ተቋም ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ፖሊስ ከየትኛውም ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ ማገልገል እንደሚገባው ጠቁመው በጠንካራ ስነ-ምግባር የዜጎችን ደህንነትና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ መንግስትም በተለይ በአደረጃጀት፣ በህግ ማዕቀፍ እንዲሁም በቴክኖሎጂ በመደገፍ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና የፖሊስ መብትና ጥቅም እንዲከበርም በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።


የክልሉ ፖሊስ እያከናወናቸው በሚገኙ ተግባራት የክልሉ ህዝቡ ድጋፉን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነስሪ ዘካርያስን በበኩላቸው እንደተናገሩት የክልሉ ፖሊስ ተቋማዊ ሪፎርም በማድረግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ከዚህ ባሻገር ሰላምን በማረጋገጥና የህግ የበላይነት በማስፈን ረገድ ፖሊስ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው በአሁኑ ወቅትም በርካታ ሰልጣኞች ተቋሙን እንዲቀላቀሉ መደረጉን ተናግረዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሐረር ቅርንጫፍ)