የገንዘብ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ


መስከረም 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር ተወያዩ።

ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ትናንት ምሽት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን በዛሬው ዕለት ከገንዘብ ሚኒስትሩ ጋር በሁለትዮሽ ትብብርና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረትን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውም ተገልጿል።

የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ የ650 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ የባለብዙ ዘርፍ የድጋፍ መርኃግብር ዛሬ ከሰዓት በኋላ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን በቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ አመራሮችና ቀጣናዊ ልዑካን ጋር ይወያያሉ ተብሏል።