ኢሬቻ የሰላምና የዕርቅ በዓል ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ኢሬቻ የሰላምና የዕርቅ በዓል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢሬቻ በዓልን አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ኢሬቻ የሰላምና የዕርቅ በዓል ነው!
ክቡር የኦሮሞ ሕዝብ ፣
ክቡራን የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣

በቅድሚያ እንኳን አስቸጋሪውን የክረምት ወቅት አልፋችሁ ውብ ወደሆነው የብራ ወቅት ተሻገራችሁ ፤ እንኳን አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ!

በማግኘት እና በማጣት፣ በጥጋብና በረሃብ፣ በስኬትና በውድቀት እንዲሁም በሙላትና በጉድለት ውስጥ ከእኛ ጋር የሆነውን ፈጣሪያችንን ማመስገን ባህላችን አድርገነዋል። ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ የምስጋና በዓል ነው ። ከሁሉም በፊት ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮችን ተቋቁመን፣ ትንሽ ትልቁን ዕንቅፋቶችን አሸንፈን ብርሃናማውን ብራን እንድናይ ያስቻለን ፈጣሪ ይክበር፤ ይመስገን!

ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንኳን አደረሳችሁ፤ እንኳን አደረሰን!
ለኢሬቻ ወደ መልካ ከመውጣት በፊት “ሰው ከፈጣሪው ጋር ሰላም ነው? ሰው እርስ በእርሱ ሰላም ነው?” የሚሉ ጥያቄዎች የተለመዱ ናቸው ። የተጣላና እላፊ የተነጋገረ፣ የተቃቃረ ሰው ለኢሬቻ ወደ መልካ ከመሄዱ በፊት እርስ በእርስ ይቅር ሊባባል ይገባል። ፈጣሪን ከማመስገን በፊት ከፈጣሪና ከፍጡራን ጋር መታረቅ የተለመደ መልካም እሴት ነው ። በኢሬቻ በዓል ርጥብ ሳር በእጅ ይዞ፣ በጀማው ውበት ታጅቦ “መሬሆ መሬሆ …” እያሉ ለፈጣሪ በሚቀርብ የውዳሴ ዜማ ወደ መልካ መትመሙ ኢሬቻ የኦሮሞ የአንድነቱ ተምሳሌትና የሰላም በዓል ነው።

በመሆኑም ኢሬቻን የሚያውቅ ሰው ቂምን ተጸይፎ ሰላምን ይሰብካል። ሰላምና አንድነት፣ ኅብረትና ወንድማማችነት መርሑ ነው ። ከፈጣሪ ለተቀበለው ክቡር ስጦታ ዕውቅና ይሰጣል። የፍጡራንን ኅብርና አብሮነት እያደነቀ ለፈጣሪ ምስጋና ያቀርባል። ድኻውን በመስጠት ይደግፋል፤ የታረዘውን ያለብሳል፤ ማዕዱን በማጋራት አብሮ ደስታን ይጋራል። በኢሬቻ ውስጥ ያለው የሰላም ትርጉም በራስ ድንበር ዙሪያ ሰላም ከመሆንና በሰላም ከመኖር ባሻገር አርስ በእርስ መደጋገፍን በውስጡ ያካትታል።

ኢሬቻ የፍትሕና የእኩልነት፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል ነው። ኢሬቻ ታላቅ ጀማን የሚሰበስብ የገዳ ጥላ ፣ ወንድማማችነትንና አብሮነትን እንዲሁም የወንድማማች ሕዝቦችን ወዳጅነት ከፍ አድርጎ የሚያሳይ በዓል ነው። በእሴቶቻችንና በባህላችን ዙሪያ ተሰባስበን፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ የሚያደናቅፉን ዕንቅፋቶችን ሁሉ በመንቀል ዛሬ ላይ ሆነን ነገን የበለጠ ብሩህ ለማድረግ ጠንክረን ልንሠራ ይገባል።

ዘመኑ የበረከትና ጥጋብ፣ የሰላምና የዕርቅ፣ ሠርተን ስኬትን የምንጎፀፍበት፣ ዘርተን በመቶ እጥፍ የምናጭድበት እንዲሆንልን እመኛለሁ። በስኬት አንገታችንን ቀና የምናደርግበት ዘመን፣ ቂምና ጉስቁልናን አሸንፈን የሕዝባችንን ዕውቀትና ታላቅነት ለዓለም የምናሳይበት ዘመን ይሁንልን።

እንደ ኢሬቻ በዓል ያለውን ታላቅ ሥርዓት አንድነታችንን የሚያጠናክር መሣሪያ አድርገን በመያዝ፣ ከቅርብም ከሩቅም በብልጽግና ጉዟችን ላይ የሚቃጣውን ወጥመድ ሁሉ ሰባብረን የያዝነውን ዓላማና ራዕይ የምናሳካበት የታሪካዊ ጉዞ ዘመን ይሁንልን።

ገዳው የጥጋብና የበረከት፣
ዘመኑ የስኬትና የድል ይሁንልን !
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 25፣ 2016 ዓ.ም