በካፋ ዞን በመኖ ማቀነባበሪያ ማሸን የተመረተ የእንስሳት መኖ ግብይት ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሄደ

ታህሳስ 14/2016 (አዲስ ዋልታ) በካፋ ዞን አድዮ ወረዳ ቦቃ ቀበሌ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ በተተከለው የመኖ ማቀነባበሪያ ማሸን የተመረተ የእንስሳት መኖ ግብይት ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሂዷል፡፡

በክልሉ የሚስተዋለውን የእንስሳት መኖ ዕጥረት ለመቅርፍ ትኩረት ሰጥተው እንደሚስሩ በካፋ ዞን ቦቃ ቀበሌ የሚገኘው የቦቃ ሹታ የቦንጋ ምርጥ ዝርያ ማሻሻያ ማህበር አባላት ገልጸዋል።

የእንስሳት መኖ አቅርቦትን ለማሻሻል የሚረዱ ዘመናዊ የአሰራር ዘዴዎችን በማቅረብ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስራዎችን ከቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን በዓለም-አቀፍ ደረጃ ደረቃማ አካባቢዎች ላይ የግብርና ምርምር የሚያደርገው ኢካርዳ /ICARDA/ አስታውቋል፡፡

በኢካርዳ የእንስሳት መኖ ተመራማሪ ሙሉቀን ዘለቀ በተቀነባበረ የመኖ ግብይት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሀገራችን የእንስሳት ምርታማነትን ከሚገቱ በርካታ ችግሮች ዋነኛው መኖ በበቂ ሁኔታ፣ በጥራትና በብዛት አለመኖር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ ችግር ደግሞ የስጋ፣ የእንቁላል፣ የወተትና መሰል ምርቶችን በበቂ መጠን የማምረቱን ስራ አዳጋች አድርጎት ሰለመቆየቱ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኢካርዳ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የመኖ ዕጥረት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ በካፋ ዞን አድዮ ወረዳ ቦቃ ቀበሌ በቦንጋ በግ ዝርያ ማሻሻያና ድለባ ለተደራጁ ዜጎች 1 ነጥብ 5 ሚለየን ብር ወጪ በማድረግ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሸን ወደ ስራ ማስገባቱ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ማሽኑ በቀን አምሳ ኩንታል የእንስሳት መኖ የማምረት አቅም እንዳለው የገለጹት ተመራማሪው በዶሮና በከብት እርባታ የተሰማሩ ግለሰቦች ከማህበሩ ጋር በመነጋገር የተቀነባበረ የእንስሳት መኖ እንዲያመርቱ ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

በቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳት ምርምር ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር እና የእንስሳት ጤና ተመራማሪ ዶክተር ናሆም በላይ ለእንስሳት እርባታ ከሚያስፈልጉ ግብአቶች የመኖ አቅርቦትና አመጋገብ ከ60 እስከ 80 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የማሸኑን አጠቃቀም በተመለከተ በተለያየ ጊዜ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በዘርፉ ለተሰማሩ ወጣቶችና ሴቶች መሰጠቱን የገለጹት ዶክተር ናሆም፤ አርሶ-አደሮች የመጣውን ዕድል በተገቢው ተጠቅመው በዘርፉ የሚስተዋለውን ውስንነት በመቅረፍ ምርትና ምርታማነቱን ሊያረጋግጥጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዘርፉ ከተደራጁ አርሶ-አደሮችና ወጣቶች መካከል አስቴር ሀይሌ፣ መብራቱ ሀይሉ እና ሌሎችም በሰጡት አሰተያየት፤ ከዚህ ቀደም ለእንስሳት በመኖነት የሚያቀርቡት በአብዛኛው በአካባቢያቸው ከሚገኝ የሰብል ተረፈ-ምርት በመሆኑ ለእንስሳት ምርታማነት በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በማህበሩ አማካኝነት በተመጣጣኝ ዋጋ የተቀነባበረ የእንስሳት መኖ መቅረቡ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ እንደሚያረጋግጥላችው ተስፋ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሸኑ ለአካባቢው አርሶ-አደሮች ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባለፈ በክልሉ ለሚገኙ አርሶ-አደሮች በቂና ጥራት ያለውን መኖ ለማቅረብ ተግተው እንደሚሰሩም ማረጋገጣቸውን ከክልሉ መገናኛ ብዙሐን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዘርፉ የተደራጁ አርሶ-አደሮችና ወጣቶች፣ የዞን እንስሳትና ዓሳ ሀብት መምሪያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በግብይት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡