በፈጸሙት የጥፋት ተግባር ተጸጽተው የበደሉትን ህብረተሰብ ለመካስ መዘጋጀታቸውን ወደ ሰላማዊ ሕይወት የተመለሱ የሸኔ አባላት ተናገሩ

ታህሳስ 14/2016 (አዲስ ዋልታ) በፈጸሙት የጥፋት ተግባር ተጸጽተው የበደሉትን ህብረተሰብ ለመካስ መዘጋጀታቸውን የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ሰላማዊ ሕይወት የተመለሱ የሸኔ አባላት ተናገሩ።

የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደሰላማዊ ሕይወት የተመለሱ የሸኔ አባላት በመንግስትና በህብረተሰቡ ላይ ለፈጸሙት በደል ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፣ በፈጸሙት የጥፋት ተግባርም ከመጸጸት ባለፈ ዳግም በመሰል ተግባራት ላይ ላለመሰማራት በሃይማኖት አባቶችና በአባ ገዳዎች ፊት ቃል ገብተዋል።

የጥፋት ተልዕኮ ወስደው በኦሮሚያ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩና ወደሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ የተደረጉት ተመላሾቹ፣ ለሁለት ወራት የተሰጣቸውን የተሃድሶ ስልጠና አጠናቀው ዛሬ ወደሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ተደርጓል።

ተመላሾቹ በፈጸሙት የጥፋት ተግባር በመጸጸት በቀጣይ ህብረተሰቡን ለመካስ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

ወደሰላማዊ ህይወት ከተመለሱት መካከል በያን ሙሜ እንዳለው የሸኔን የጥፋት ተልዕኮ ሲያራምድ በነበረበት ወቅት በህዝብና በአገር ላይ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል።

“እኛ ምንም በማናውቀው የጥፋት ተግባር ተሰማርተን በደል ስንፈጽም ብንቆይም፤ አሁን ከድርጊቱ ተቆጥበን ህዝብና መንግስትን ለመካስ ተዘጋጅተናል” ሲልም ገልጿል።

“ሸኔ በሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመጠቀም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ለማጋጨት የሚሰራ ነው” ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ ተመላሽ ጫልቱ አብዱረህማን ናት።

“የጥፋት ተልዕኮን በማንገብ የተለያዩ ተግባራት ስናከናውን ነበር” የምትለው ጫልቱ፣ ወደቀዬዋ ስትመለሰ በደል ያደረሰችበትን ህዝብ ለመካስ እንደምትሰራ ተናግራለች።

“ሸኔ በሰው ህይወት፣ በመንግስት እና በህዝብ ንብረት ላይ አረመኔያዊ ድርጊት ሲፈጽም ነበረ” ያለው ደግሞ ሌላው የተሀድሶ ስልጠና የወሰደው አህመድ አደም ነው።

የሸኔ አባል በነበረበት ጊዜ በፈጸመው እኩይ ተግባር መጸጸቱንና ዳግም በተመሳሳይ የጥፋት ተግባር እንደማይሰማራ ያረጋገጠው አህመድ፣ ሌሎች የሸኔ አባላትም ከጥፋት ተግባር ወጥተው እጃቸውን ለመንግስት በሰላም እንዲሰጡ ጠይቋል።

በእለቱ የተገኙት አባ ገዳ አብዱማሊክ ጁንዲ በበኩላቸው ወጣቶቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰው ህብረተሰቡን ለመካስና በቀጣይ ሥራ ፈጥረው ለመንቀሳቀስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ ነው ያሉት አባገዳ አብዱማሊክ፣ ሌሎች ወጣቶች አገርን ከማይጠቀምና ከሚያፈርስ ተግባር ራሳቸውን ማራቅ እንዳለባቸው መምከራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሚስኪ መሀመድ በበኩላቸው፣ ወጣቶቹ ከፈጸሙት ጥፋት ተጸጽተውና ተምረው ህብረተሰቡን ለማገልገል ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።

እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ ሰጥተው የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች በአካባቢያቸው በልማት ሥራ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በዞኑ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

“ለአገር የሚበጀው ዘላቂ ሰላም እና እንድነት ነው ያሉት” ዋና አስተዳዳሪዋ ሌሎች የሸኔ አባላትም ከጥፋት ተግባር ወጥተው የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።