የካቲት 14/2016 (አዲስ ዋልታ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ዋሻ የተናደባቸውን የማዕድን አውጪ ሰራተኞችን ለማውጣት የሚደረገው ቁፋሮ እስከ 120 ሜትር እንደሚቀረው ተገለጸ፡፡
የደላንታ ወረዳ ማዕድን ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተስፋ ሰማሁ ከአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ በሰው ኃይል ሲደረግ የነበረው ቁፋሮ በመሬት መንሸራተትና የዋሻው የታችኛው ክፍል በሚቆፈርበት ወቅት ይደረመሳል በሚል ስጋት ቆሞ ነበር፡፡
በመሆኑም ከሰው ኃይል በዘለለ አካባቢውን በድማሚት ለማፍረስ ሙከራ የተደረገ ሲሆን ይህም ተራራው ሊናድ ይችላል የሚለውን ስጋት እንዳስቀረ ጠቁመዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በሰው ኃይል የሚደረገው ቁፋሮ ዳግም ቀጥሏል ብለዋል፡፡
በዚህም እስካሁን 80 ሜትር ያህል ቁፋሮ መካሄዱን የጠቆሙት ኃላፊው ሰራተኞቹ ምንአልባትም እስከ 200 ሜትር ጥልቀት ውስጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ሰራተኞቹን ለማግኘት እስከ 120 ሜትር ቁፋሮ እንደሚቀርም አመልክተዋል፡፡
ሰራተኞቹን በህይወት የማግኘት እድል ምንያህል ነው ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄም እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው ነገር የለም ያሉ ሲሆን ነገር ግን ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ወረዳ ዋሻ የተደረመሰበት የማዕድን ሰራተኛ ከ11 ቀናት ቁፋሮ በኋላ በህይወት መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ተደጋጋሚ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለሰራተኞቹ የግንዛቤ ማስጨባጫ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው አሁን ያሉትን ሰራተኞች ለማውጣት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ሁሉም የሚመለከተው አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 6 ሰዓት ገደማ በደላንታ ወረዳ ልዩ ስሙ ቆቅ ውሃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በባህላዊ መንገድ የኦፓል ማዕድንን በማውጣት ላይ የነበሩ ወጣቶች ባጋጠማቸው የመሬት መደርመስ አደጋ በፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረው ከቆዩ ዛሬ ሁለተኛ ሳምንት ተቆጥሯል፡፡