የኢትዮጵያን ሁለትዮሽ ትብብርን የሚያሳድጉ የተለያዩ ስምምነቶች ከተለያዩ ሀገራት ጋር መፈረማቸው ተገለጸ

አምባሳደር መለስ አለም

የካቲት 14/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያን ሁለትዮሽ ትብብርን የሚያሳድጉ የተለያዩ ስምምነቶች ከተለያዩ ሀገራት ጋር መፈረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ከአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝ ከደቡብ አፍሪካ፣ አንጎላ፣ ዝምባብዌ እና ኬንያ ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።

ለደቡብ አፍሪካ ነጻነት የኢትዮጵያ ሚና የጎላ መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ ይህን በሚያጸና መልኩ ትብብርን ለማሳደግ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ከአንጎላ ጋር በተደረገው ስምምነት ሀገሪቷ በነዳጅ የምትታወቅ እንደመሆኗ ልምድ የምንወስድ ይሆናል ያሉት አምባሳደር መለስ ከዝምባብዌ ጋር በግብርናና በሌሎች መስኮች በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ኬንያ የሚኒስትሮች ስብሰባ መካሄዱን ጠቅሰው ሀጋራቱ በሰባት ዘርፍች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

የቪዛ ጉዳይ ሌላኛው ስምምነት መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ በ1958 ዓ.ም የተደረገው የቪዛ ነፃ ስምምነት በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መልኩ እንዲሆን መከለሱንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያም የተለያዩ ለቱሪስት መስህብ መሆን የሚችሉ ተፈጥሯዊና ተፈጥሯዊ ያልሆኑ የቱሪስት መዳረሻ እንዳላት ገልጸው በዚህም ከኬንያ ጋር ልምድ በመቅሰም የተሻለ አቅም መፍጠር ይቻላል ተብሏል።

በመስከረም ቸርነት