መጋቢት 3/2016 (አዲስ ዋልታ) በአማራ ክልል የሚስተዋለውን ግጭት ለመቆጣጠርና በዘላቂነት ለመፍታት ምክክርና ንግግር እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም ገለጸ።
ተቋሙ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ጋር በመተባበር በአማራ ክልል እየተስተዋለ የሚገኘውን ግጭት ማስቀረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኬይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ የሰላም መደፍረሶች ከንግግር ይልቅ በኃይል ለመፍታት በመሞከር የመነጩ ናቸው ብለዋል።
ይህ አካሄድ ችግሮችን እያባባሰና አንድነትን እያደፈረሰ ከመሄድ ውጪ የሚያመጣው መረጋጋት እንደማይኖር የገለጹት ሚኒስትር ዴታው በመሆኑም የተፈጠሩትን የሀሳብ ልዩነቶች ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሰላምን ለማስፈን የግጭት መንስኤዎችና መፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መንግስት ጥናቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው ይሁንና ሰላም በመንግስት ጥረት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ሁሉም ግለሰቦችና ተቋማት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አሁንም ድረስ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሆኑ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡና ሀሳባቸውን በሰለጠነ መንገድ እንዲያንሸራሽሩ በሩ ክፍት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በታምራት ደለ