አገራዊ ለውጡ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከነበረበት ውስብስብ የግንባታ ሂደት በማውጣት ለስኬት እንዲበቃ አድርጓል – ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

መጋቢት 4/2016 (አዲስ ዋልታ) አገራዊ ለውጡ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ከነበረበት ውስብስብ የግንባታ ሂደት በማውጣት ለስኬት እንዲበቃ ማድረጉን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ከአገራዊ ለውጡ በፊት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦበት ወደ መቆም ደርሶ እንደነበር አስታውሰው በተለይም ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ የሚሰጡት ገንዘብ አቅም በሌለው ተቋራጭ የግንባታው ሂደት እንዲመራ መደረጉና የተሰበሰበው ገንዘብ ሲመዘበር መቆየቱን ተናግረዋል።

ይህ ተገቢ ያልሆነ የፕሮጀክት አስተዳደርና ሆን ተብለው የተፈጸሙ ብልሹ አሠራሮች በግንባታው አጠቃላይ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረሳቸውንና ይህም አሳዛኝ ክስተት እንደነበር ነው ያነሱት።

እንዲያም ሆኖ በአገራዊ ለውጡ ማግስት የግድቡን ቀጣይ ሂደት ለመወሰን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተከናወነው ይኸው ሥራ ግድቡን ከገባበት ችግር በማውጣት ረገድ ትልቁ የስኬት መነሻ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግድቡ ባደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት የፕሮጀክቱን ዕጣ-ፈንታ ለመወሰን የወሰዱት ጥበብ የተሞላበት አመራር ትልቁ የስኬት ጉዞ መጀመሪያ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የፕሮጀክቱ ትልቅ ችግር የነበረውን የኮንትራት አስተዳደር እንዲሁም ተቋራጮችንና ዕቃ አቅራቢዎችን መቀየር የመጀመሪያ እርምጃ እንደነበር አንስተው በዘርፉ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን የመመደብ ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል።

በእነዚህም ተግባራት አገራዊ ፕሮጀክቱን ተደቅኖበት ከነበረው አደጋ መታደግ መቻሉን ጠቅሰው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሕዳሴ ግድብ የተሰሩት ሥራዎች ግድቡን ዳግም የማስጀመር ያህል ድል የተመዘገበበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከአገራዊ ለውጡ በፊት ፕሮጀክቱ ለስም የተቀመጠ እንጂ ተጨባጭ ሥራዎች እንዳልነበሩበት የገለጹት ሚኒስትሩ ከለውጡ ወዲህ ሕዝቡ በየዓመቱ የሚቆጠርና የሚለካ ውጤት ማየቱን ተናግረዋል።

ለአብነትም ሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻላቸውን የአገራዊ ለውጡ ስኬት ማሳያ መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት።

ግድቡ የኢትዮጵያውያንን ከፍታ የሚያረጋግጥ መሆኑን ያወቁ አካላት ግድቡ ሲጀመር ያላሰሙትን ጩኸት በለውጡ ማግስት ማሰማታቸውን አንስተው ይህም ሲጀመር አይጠናቀቅም የሚለው እምነታቸው በለውጡ አመራር ስለከሸፈ መሆኑን ጠቁመዋል።

በርካታ ውጣ-ውረዶችን ያለፈው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አሁን ላይ ቁመቱን ከመጨመር አልፎ በተለያዩ ዙሮች የውኃ ሙሌት በማድረግ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ግድቡ አሁን ላይ ማንም ወደኋላ ሊቀለብሰው በማይችልበት ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ትምህርት በሚሰጥ ደረጃ መገንባቱን ነው ያስረዱት።

ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩና በጋራ ከቆሙ ተአምር መሥራት እንደሚቻል ያስተማረ ትልቅ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በለውጡ አመራር ግድቡ ዛሬ ላይ ለስኬት መብቃቱን ገልጸው አጠቃላይ የግንባታው ሂደት 95 በመቶ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመት ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ግድቡ ውኃው መያዝ ያለበትን ቁመት የመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደሚደርስ አመላክተዋል።