ኢትዮጵያና ፓኪስታንን በተለያዩ ዘርፎች በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ


መጋቢት 4/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያና ፓኪስታንን በተለያዩ ዘርፎች በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

በኢትዮጵያና በፓኪስታን መካከል ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፓኪስታኑ አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ጋር በሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ዙሪያ በተወያዩበት ወቅት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ እና የፓኪስታን ሁለንተናዊ ትስስር ታሪካዊ መሆኑን አስታውሰው ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ሁለቱም ሀገራት ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች በንግድ፣ በጤና፣ በኢንቨስትመንት፣ በባህል እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን በበኩላቸው በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት፣ የትምህርት፣ የኢኮኖሚ፣ የባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ትስስር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በትምህርት፣ በጤና እና በኢንቨስትመንት ልማት ዘርፍ ፓኪስታናዊያን ባለሃብቶች እና ምሁራን በስፋት እየሰሩ እንደሚገኙና በቀጣይነትም ይህን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የሁለቱን ሀገራት ፓርላሜንታዊና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንዲረዳ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔዎች ፓኪስታን ተገኝተው ከፓኪስታን የፓርላማ አባላት ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉም መጠየቃቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡