ባለስልጣኑ በወደቦች የተከማቹ ኮንቴነሮች በአገልግሎት ላይ ውስንነት እየፈጠሩበት መሆኑን አስታወቀ

በጉምሩክ ወደቦች ተከማችቶ የሚገኙ ኮንቴነሮች ለረዠም ጊዜ የሚቆዩና ንብረቶቹ በፍጥነት የማይነሱ በመሆኑ  በአገልግሎት አሠጣጥ ላይ ውስንነት እየፈጠረበት መምጣቱን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስመጪዎች እና ላኪዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መድረክ የተካሄደ ሲሆን ተሳታፊዎቹ መስሪያ ቤቱ አሰራሩን በማዘመንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመሥጠት ማገልገል እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ቴክኖሎጂን በአግባቡ ያለመጠቀም ሁኔታ በመስሪያ ቤቱ እንደሚስተዋልም ጠቁመዋል፡፡

መስሪያ ቤቱ ከመድረኩ ተሳታፊዎች የተነሱ ጉዳዮችን በግብዓትነት ወስደው በቀጣይ ትኩረት በመስጠትና የአሰራር ማዕከል በማድረግ እንደሚተገብር የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡመር ሁሴን ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሶስት ወርና ከዛ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ቋሚ ግንኙነት በመፍጠር በአሰራሮች ዙሪያ ግብረመልስ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡

በባለሀብቶቹ በኩል የዕቃ ዝርዝር መረጃዎችን በበቂ ሁኔታ አደራጅቶ አለመያዝ እና ዕቃዎችን ለማስገባት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ያለማሟላት የሚታዩ ክፍተቶች እንደሆኑ እና ይህንንም ማረም እንደሚገባቸው አቶ ኡመር አስገንዝበዋል፡፡