ኢንጂነር ታከለ ኡማ የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከልን በይፋ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ መርቀው ከፈቱ

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከልን በይፋ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሠጥ መርቀው ከፍተዋል፡፡

የዕፅዋት ማዕከሉ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት መሆኑን ለማብሰር በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የተገኙት ኢንጂነር ታከለ ኡማ የጉለሌ የፅፅዋት ማዕከል ለከተማዋ ህዝብ ተጨማሪ ሃብት መሆኑን ተናግረዋል ።

በከተማዋ ዳርቻ ላይ ያለውን የጉለሌ እጽዋት ማዕከል አረንጓዴ ፀጋ ወደ መኃል ከተማ ለማምጣት የከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለሚቀጥሉት 6 ወራት የዕፅዋት ማዕከሉ ጎብኚዎችን የሚያስከፍለውንም ክፍያ የከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፍን እና የከተማዋ ነዋሪ ያለምንም ክፍያ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ማዕከሉን መጎብኘት እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

እጥዋት ማዕከሉ ለከተማው ህዝብ የመናፈሻነት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በተጨማሪም በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎች እንክብካቤ ተግባራትን ማከናወን፣ በስነ ህይወት፣ በተፈጥሮ ሃብት አያያዝ እና በሌሎች አከባቢ ነክ መስኮች ላይ ምርምር ይካሄድበታል ነው የተባለው፡፡

በአጠቃላይ 705 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የዕፅዋት ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለበርካታ የከተማ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

 (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)