ቤጉህዴፓ አቶ አድጎ አምሳያን ሊቀመንበር አድርጎ ሾመ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አቶ አድጎ አምሳያን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ ሾመ፡፡

አዲሱ የቤጉህዴፓ ሊቀመንበርም በዚሁ ወቅት የሃሳብ አሸናፊነትን በክልሉ ለማስፈን እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

“ለህዝብ እና ለድርጅቱ መርሆች ቅድሚያ እሰጣለሁ”ያሉት አቶ አድጎ ከማዕከላዊ ኮሚቴው ጋር በመደጋገፍ የህብረተሰቡን ህይወት መለወጥ ይቻላል ብለዋል፡፡

በአስቸኳይ ጉባኤው ላይ የተሰጧቸውን ገንቢ አስተያየቶች እንደ ግብዓት እንደሚጠቀሙ ገልጸው በቀጣይ የስራ ዘመናቸው ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ህዝብን በሚጠቅሙ ስራዎች ላይ እንደሚያተኩሩ አስረድተዋል።

በፍላጎታቸው ኃላፊነታቸውን ለለቀቁት የቀድሞው የቤጉህዴፓ ሊቀመንበር አቶ አበራ ባዬታ ውሳኔ አክብሮታቸውን ጠቅሰው የሳቸው ድርጊት ለሌሎች አባላት በአርአያነት የሚጠቀስ እንደሆነ ተናግረዋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በተጓደሉ ሶስት የፓርቲው ስራ አስፈጻሚዎች ምትክ አቶ አወቀ አይሸሽም፣ አቶ ቀልቤሳ ኦልጅራ እና ወይዘሪት ምስኪያ አብደላን መርጧል።(ኢዜአ)