በ125ኛው የአለም ፓርላማዎች ህብረት ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ፓርላማ የልኡካን ቡድን ወደ አገሩ ተመለሰ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2004/ዋኢማ/ – በ125ኛው የአለም ፓርላማዎች ህብረት ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ፓርላማ የልኡካን ቡድን ወደ አገሩ ተመለሰ።

በሲውዘርላንድ በርን ከተማ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ፓርላማ የልኡካን ቡድን ስምንት አባላትን ያቀፈ ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና የልኡካን ቡድኑ መሪ ካሳ ተክለብርሐን በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫ የአለም ፓርላማዎች ህብረት ጉባኤ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ ግንባታ፣ አረንጓዴ ልማትና ጤና በዋናነት የመከረባቸው ጉዳዮች ናቸው።

የአለም ፓርላማዎች ህብረት ጉባኤ የኤርትራ መንግስት ከዚህ ቀደም በአገሪቱ የነበሩትን የብሄራዊ ሸንጎ አባላት ያደረሰበት ባለመታወቁና በሌሎች አባላት ላይም እየፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ክፉኛ ማውገዙን አፈ-ጉባኤው አስረድተዋል።

ስምንት አባላትን ያቀፈው የኢትዮጵያ ፓርላማ የልኡካን ቡድን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከህንድና ከጃፓን ፓርላማ የልኡካን ቡድን አባላት ጋር በአገሮቹ የጋራ ጉዳዮች፣ በኢንቨስትመንት፣ በመልካም አስተዳደርና በአለም አቀፍና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጉን አብራርተዋል።

የልኡካን ቡድኑ በተለይ በኢትዮጵያና በሲውዘርላንድ የፌዴራል መንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይም ምክክር ያደረጉ ሲሆን፤ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ለማሳደግም ስምምነት ተደርሷል።

125ኛው የአለም ፓርላማዎች ህብረት ጉባኤ በስዊዘርላንድ በርን ከተማ የተካሄደው ከጥቅምት 7 ቀን 2004 ጀምሮ ለ4 ቀናት ነበር።

ኢትዮጵያ የአለም ፓርላማዎች ህብረት አባል የሆነችው እ.ኤ.አ ከ1954 ጀምሮ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በ2001 ዓ.ም 120ኛውን የአለም ፓርላማዎች ህብረት ጉባኤ ማስተናገዷ ይታወሳል።