የዓለም የምግብ ፕሮግራም በ72 ወረዳዎች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስና የአፈር ጥበቃ እንክብካቤ ስራ እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2004/ዋኢማ/ – በሀገሪቱ በ72 ወረዳዎች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስና የአፈር ጥበቃ እንክብካቤ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።

የፕሮግራሙ ተወካይ አቶ ፍስሀነገስት ገብሩ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ፕሮግራሙ የአፈር ጥበቃና እንክብካቤ ስራውን የሚያከናውነው በመሬት ፕሮጀክት አማካኝነት ሲሆን፤ በ72 ወረዳዎች ከ600 በላይ ሳይቶች ላይ የልማት ስራውን እያከናወነ ነው።

ፕሮጀክቱ በአማራ 23 ወረዳዎች፣ ትግራይ 17፣ በኦሮሚያ 16፣ በደቡብ 12፣ በሱማሌ 3 ወረዳዎችና በድሬዳዋ 1 ወረዳ ላይ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የአፈር ጥበቃና እንክብካቤ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የመሬት ፕሮጀክት የየአካባቢውን ህብረተሰብ በሴፍቲኔት በማሳተፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ስራውን ቀደም ባሉት አመታት ለድርቅ የተጋለጡ የነበሩ አካባቢዎች መልሶ የማልማት ስራውን አጠናክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመሬት ፕሮጀክት የህብረተሰቡን አቅም በመገንባትና ግንዛቤያቸውን በማሳደግ፣ የእርሻ መሳሪያ በማቅረብ፣ የሞተር ብስክሌትና የተለያዩ የችግኝ ማፍያዎችን በማቅረብ ስራውን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያም 33ሺ ቶን እህልና 500 ሺ ዶላር ለአቅም ግንባታ ወጪ መደረጉን ተወካዩ አቶ ፍስሀነገስት ገብሩ ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ ስራውን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የተፋሰስ ስራዎችን ሲያካሄድ እንደነበር ጠቁመው፤ ከ1995 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ግን የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ አመርቂ ውጤት ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ለ30 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የአፈር ጥበቃና እንክብካቤ ስራ የሚያስፈልጋቸውን ቦታዎች በመለየት የማልማት ስራ ሲሰራ እንደነበር ጠቁመው፤ በሚቀጥለው የፈረንጆች አመት ፕሮጀክቱ ስራውን እንደሚያጠናቅቅ ገልፀዋል።

ሆኖም ፕሮጀክቱን ከአለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በአዲስ መልክ ለአራት አመታት ለማስቀጠል መታቀዱን ፍስሀነገስት ገብሩ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።