በክልሉ በተካሄደ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም አመርቂ ውጤት መገኘቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2004/ዋኢማ/-ባለፉት አመታት በክልሉ በተካሄደ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም አመርቂ ውጤት መገኘቱን የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ጓነር የር የክልሉ የ2004 የበጀት ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ የክልሉን የገጠር ህዝብ በመንደር በማሰባሰብ የመሰረተ ልማት አውታሮችና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዲሆን በተደረገው እንቅስቀሴ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

ነዋሪዎችን በመንደር የማሰባሰቡ ተግባር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማሳኪያ ዋንኛ መሳሪያ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህዝቡ በአጭር ጊዜ እራሱን ከድህነት እንዲያላቅቅ በማድረግ ትላንት በቁጭት፣ ዛሬ በጥረትና ነገን ደግሞ በስኬት እንዲያስብ ሰፊ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመደጋገፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ መዘጋጀቱን በምክክር መድረኩ ላይ የተገለፀ ሲሆን፤ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ምን እንደሚጠበቅባቸው የምክክር መድረኩ መካሄዱ እንደሚጠቅም አስታውቀዋል፡፡

መድረኩን የመሩት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም በበኩላቸው፤ በክልሉ ያለውን የግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ውሃና በሲቪል ሰርቪስ የተያዙ ወሳኝ ግቦችን ዘጠና በመቶ ለማሳካት የልማት ስራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ማካሄድና በክልሉ ያለውን የአቅም ክፍተት ማጥበብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ በ43 መንደሮች ከ26ሺ በላይ ቤተሰቦችን ማስፈር የተቻለ ሲሆን፤ ከፌዴራልና ከክልሉ የተወጣጡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በአቦቦ ዞን በሚገኙ የተለያዩ መንደሮችን መጎብኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።