ዩኒቨርስቲው ሁለት አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች ማስተማር ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2004/ዋኢማ/ – የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በሚቀጥለው አመት በሁለት አዳዲስ የትምህርት ዘርፍ ማስተማር ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወንድሙ ገብሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ወቅት ከሚሰጠው 34 የትምህርት ዘርፍ በተጨማሪ በሜዲካል ዶክትሬትና በኢኮ-ቱሪዝም የትምህርት ዘርፍ ማስተማር ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ነው።

ዩኒቨርስቲው በ1999 ዓመተ ምህረት የተቋቋመ ሲሆን፤ ሲጀምር የነበረውን የተማሪዎች ቅበላ ከ250 ወደ 8ሺ ከፍ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ወቅት ስምንት ሺ የሚገመቱ ተማሪዎች በቀንና በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተቀብሎ እያስተማሪ ሲሆን፤ ማስተማር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን 2ሺ 600 ተማሪዎችን አስተምሮ ማስመረቁን ተናግረዋል። 

ዩኒቨርስቲው በተለይም በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ የቅመማ ቅመምና የግብርና ምርቶችን ለማሻሻል የሚያስችል የተለያዩ የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በዚህም በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን አቅም በማሳደግ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጥረት እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

እንዲሁም በአካባቢው ከ640 ሺ ሄክታር በላይ ለተፋሰስ የተጋለጡ አካባቢዎችን በመለየት የተቀናጀ የተፋሰስ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚያደርገው እንቅስቃሴም 8 ሚሊየን ብር የሚገመት የተለያዩ የመማር ማስተማር ቁሳቁሶችን ከውጪ በመግዛት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን ጠቁመው፤ በዩኒቨርስቲው የሚገኙ ቤተመፃህፍትም 24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ተናግረዋል።

እንዲሁም አዲስ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው ሲገቡ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጣቸው አቶ ወንድሙ መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።