በደቡብ ክልል የተገነቡ 229 የትምህርት ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

ሀዋሳ ጥቅምት 17/2004/ዋኢማ/– በደቡብ ክልል ባለፈው የበጀት ዓመት የተገነቡ 229 የትምህርት ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ::

ቢሮው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው፤ ለአገልግሎት የበቁት የትምህርት ተቋማት ቀደም ሲል ትምህርት ቤት ባልተስፋፋባቸው የገጠር ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ  ነው::

ለአገልግሎት ከበቁት የትምህርት ተቋማት መካከል 204ቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆኑ፤ 25ቱ ደግሞ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን በቢሮው የመንግሥት ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ደረሰ ጋቲሶ ገልጸዋል::

ለአገልገሎት ከበቁት የትምህርት ተቋማት መካከል 88 በመቶ ያህሉ በክልሉ የገጠር አካባቢዎች የተገነቡ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ደረሰ በአሁኑ ወቅት ለተቋማቱ አስፈላጊው የመምህራን ቅጥር የመፈጸምና የማስተማሪያ ቁሳቁሶችን የማሟላት ሥራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል::

ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የክልሉ መንግሥትና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ከመደቡት በጀት በተጨማሪ ሕብረተሰቡ የጉልበትና አካባቢያዊ የግንባታ ቁሳቁሶችን በማቅረብ መሳተፉን የሥራ ሂደት ባለቤቱ አስረድተዋል::

ትምህርት ቤቶቹ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው የክልሉን የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ሽፋን ከ97 ወደ 103 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋንን ደግሞ ከ34 ወደ 40  በመቶ እንደሚያሳድጉት አብራርተዋል ::

በክልሉ የሚያቋርጡ ተማሪዎች መጠንን ለመቀነስ እና የትምህርት ክፍለ ጊዜ ብክነትን ለማስቀረት በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ጽሕፈት ቤት አመራሮች መምህራን ወላጆችና ተማሪዎች ባቋቋሟቸው የጋራ መድረኮች አማካኝነት ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል::

በቀጣይ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት በሙሉ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለማስመዝገብ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የሕዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር የሚያስችል ስትራቴጂ ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ማስረዳታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል::