አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2004/ ዋኢማ/– የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ልማት እንዲሳተፉ የሚያስችል የዳያስፖራ ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ ይፋ አደረገ፡፡
በሚኒስቴሩ የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ሙሉጌታ ከሊል ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አዲሱ ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ ይፋ የተደረገው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ በንግድና ኢንቨስትመንት የሚያደርጉት ተሳትፎ እያደገ በመምጣቱ ነው፡፡
ረቂቅ ሰነዱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ የኢንቨስትመንትና የልማት እንቅስቃሴ ይበልጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም በአገሪቱ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በተመለከተ በቂና ወቅታዊ ኢንፎርሜሽን ለማድረስ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት መንግሥት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉና ልምዳቸውንና ያፈሩትን ሃብት ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለአገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ረቂቅ ሰነዱን በተለይም ለዳያስፖራው ለውይይት ለማቅረብ በያዘው ዕቅድ መሰረት ኢትዮጵያውያን በብዛት ይኖሩባቸዋል ተብለው በተመረጡት በአሜሪካ 11 ከተሞች፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውስትራሊያና በአፍሪካ በጠቅላላው በ22 ከተሞች ከነገ ጀምሮ እስከ ጥር ወር መጨረሻ ውይይት ለማካሄድ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች በሚዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ዳያስፖራው ተገኝቶ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከ15 ሺህ በላይ የዳይስፖራ አባላት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።