ቢሮው የመማሪያ መጽሐፍቶችን እጥረት ለማቃለል እየሠራ ነው

ሀዋሳ ህዳር 6/2004/ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል የሚታየውን የመማሪያ መጽሐፍቶች እጥረት ለማቃለል የ28 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ መፅሀፍህት ማሳተሙን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ::

በቢሮው የመንግስት ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ደረሰ ጋቲሶ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው፤ በ28 ሚሊዮን ብር ወጪ የታተመው የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ መጽሐፍቶች መፅሀፍት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የሚታየውን የመማሪያ መጻሐፍቶች እጥረት ለማቃለል ቢሮው በጀት በመመደብ የተጨማሪ መጽሐፍቶች ህትመት ማካሄዱንም ተገልጿል።

የታተሙት የመማሪያ መጽሀፍቶች በ2004 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በጥቅም ላይ እንዲውሉ በክልሉ በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች መሠራጨታቸውን አመልክተዋል::

ታትመው ከተሠራጩት መጽሐፍቶች መካከል በተለያዩ የብሄረሰብ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የተፈጥሮና የማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት አይነቶች እንደሚገኙበት አስረድተዋል::

የመጽሐፍቶቹ መታተምና መሠራጨት የክልሉን የመማር ማስተማር ሂደት ለማቀላጠፍና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ሥራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችል የሥራ ሂደት ባለቤቱን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል::