ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ አመራር ተወካዮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2004/ ዋኢማ/ – ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ አመራር ተወካዮች ጋር ተወያዩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው ከአመራር አባላቱ ጋር ያደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢሕአዴግና በአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ መካከል የአቅም ግንባታዎችን ለማሳደግ፣ ልምድ ለመለዋወጥና ለጋራ ጥቅሞቻቸው በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ሊሰሩ የሚችሉባቸውን ጉዳዮች መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት፣ ድህነትን ማጥፋት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ የሁለቱ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ገጽታዎችና ትኩረቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ አካባቢዎች መሬት ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል በማድረግ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ አስታውቀዋል፡፡

በገጠር አካባቢዎች ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ግንኙነቶቻቸውን ለማጠናከርና የልምድ ልውውጥ በማድረግ ከአሕጉሩ ተመሳሳይ ፓርቲዎች ጋር በአንድነት ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አመልክተዋል፡፡

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ ግዌዴ ማንታሼ በበኩላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ያካሄዱት ውይይት ሁለቱ ፓርቲዎች ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮ በመቀመር ልምድ ለመለዋወጥና ወደፊት የሁለትዮሽና የብዙዮሽ ግንኙነትን ለማሳደግ ያስቻለ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ኤኤንሲ እና የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢሕአዴግ ተራማጅ ፓርቲዎች በመሆናቸው ለየአገሮቻቸውና ለአሕጉሩ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡