የአማራ ክልል ህዝብ ሰላሙን እንዲጠብቅ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ

የአማራ ክልል ህዝብ መንግስት በክልሉ ሰላምን ለማስፈን እያደረገ ላለው ጥረት ስኬት አጋዥ ሚናውን መወጣት አለበት ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ።  
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግስት ሰሞኑን በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከህዝቡ እየተነሱ ላሉ ጥያቄዎች ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።  
ህብረተሰቡም የስጋትና መረበሽ መንፈስ እንዲያድርበት ሆኖ ስንብቷል፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴውም  ተጎድቷል  ያሉት አቶ ገዱ   ችግሩ በህብረተሰቡ ላይ ቀውስ እየፈጠረ በመሆኑ መንግስት  ይህን እንደማይሻ ገልፀዋል። 
የኢትዮያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር /ኢህአዴግ/ አመራሮች ህዝቦች የሚያነሷቸውን  ጥያቄዎች በሕገ መንግስቱ መሰረት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝርዝር ግምገማ በማካሄድ ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ የሚፈቱበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል ብለዋል። 
አቶ ገዱ አያይዘውም የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን ሰላም ለማስጠበቅና የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎች  ጋር ውይይት እንደተደረገም ጠቁመዋል።
በሰላም አስፈላጊነትና የህግ በላይነት ላይ መግባባት ለማምጣት ጥረት መደረጉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። 
የክልሉም ሆነ የሀገሪቱን ሰላም ለማወክ በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ጸረ ሰላም ሃይሎች መሰረተቢስ  ወሬ እየነዙ መሆኑን ጠቁመው በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች የአገሪቱ የፍትህ ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት እንደሚፈጸም ተናግረዋል።