በየመን በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩ 10 ህፃናት ተገደሉ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 9/2008 (ዋኢማ) – በየመን በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ ጥቃት 10 ህፃናት ለህልፈት መዳረጋቸው ተሰማ።

በሀውቲ አማፂያን ይዞታ ይገኛል በተባለው ትምህርት ቤት ላይ የደረሰው የአየር ላይ ጥቃት ከ30 በላይ ህፃናትንም ለጉዳት ዳርጓል።

ድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን እንዳስታወቀው፤ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ህጻናት እድሜያቸው ከ8 እስከ 15 አመት ይደርሳል ፡፡

ጥቃቱ በሰሜን ምዕራብ ሳዳ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ሀይደን ትምህርት ቤት እየተማሩ በነበሩ ተማሪዎች ላይ መድረሱንም ቡድኑ አመላክቷል።

የሀውቲ አማፂ ቡድን ቃል አቀባይ መሀመድ አንደል ሳላም የሳኡዲ መራሹ ጥምር ጦር በትምህርት ቤቱ ላይ ጥቃት አድርሷል ብሏል።

ይሁን እንጂ የጥምር ጦሩ ከሀውቲ ታጣቂ ቡድን ለተሰነዘረው ወቀሳ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በያዝነው የፈረንጆቹ አመት አራት ወራት ብቻ በየመን ግጭት 272 ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ማስታወቁ ይታወሳል–    ( ኤፍ ቢ ሲ) ።