ውሃን ማዕከል ያደረገና ህዝቡን ያሳተፈ የመንደር ማሰባሰብን መተግበር ወሳኝ ነው -አብዴፓ

በአፋር ብሔራዊ ክልል ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ውሃን ማዕከል ያደረገና ይበልጥ ህዝቡን ያሳተፈ እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ መሆኑን የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) አስታወቀ ።   

የአብዴፓ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አምባሳደር ሐሰን አብዱል ቃድር ለዋልታ እንደገለጹት የኢህአዴግ አጋር ድርጅት የሆነው አብዴፓ ባለፉት 15 ዓመታት በክልሉ  በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ  ተግባራትን በመገምገም የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል ።

አብዴፓ የኢህአዴግ ምክር ቤት ያስተላላፋቸውን ውሳኔዎች  መሠረት በማድረግ በተለይም  በልማት ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም የታዩ ክፍተቶችን በመለየትና በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል ።

ባለፉት 15 ዓመታት የክልሉ አርብቶ አደር ህብረተሰብ በተገኘው የሰላምና ዴሞክራሲ የሚጠበቀውን ያህል በልማት ተጠቃሚ አለመሆኑ አብዴፓ መገምገሙን የጠቆሙት አምባሳደሩ በተለይ በክልሉ ተግባራዊ የሆነውን የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም በአዲስ መልክ እንዲጀመር ተወስኗል ብለዋል ።

በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ውሃን ማዕከል ያላደረገና ህዝቡን በበቂ ሁኔታ ያላሳተፈ በመሆኑ የክልሉን አርብቶ አደር ማህበረሰብ ኑሮ እንደሚፈለገው መለወጥ አለመቻሉን ባለፉት 15 ቀናት አብዴፓ ባካሄደው ግምገማ አመልክቷል ።

ለወደፊቱም የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሙን የተቀናጀ ለማድረግ የጎሳ መሪዎችን ፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፣ የአብዴፓ አመራሮችና ህዝቡ በተገኘበት የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ጭምር የተቀናጀ የመንደር ማሰባሰብን ለማካሄድ ሰሞኑን አቅጣጫ ተቀምጦ ሥራ ተጀምሯል ።

ከአገልግሎት አሠጣጥ ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት ለመፍታት   የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮችን መዘገጃታቸውን የጠቆሙት አምባሳደሩ የአመራር ቁርጠኝነት  በማይታይባቸው አመራሮችን ጭምር ለመታገል አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል ።

በመጨረሻም የአፋር ክልል ህዝብ ባለፉት 25 ዓመታት በፌደራላዊ ሥርዓቱ በርካታ የልማት ድሎችን ማስመዝገቡን በመጠቆም በክልሉ የተያዙ የልማት ዕቅዶችን በሙሉ እንዲፈጸሙ የክልሉ መንግሥትናህዝብ ይበልጥ እንደሚረባረብ አምባሳደሩ መናገራቸው ዋልታ ኢንፎሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።