በዓሉ “አሁንም ትኩረት ለኤችአይቪ መከላከል!” በሚል ቃል እየተከበረ ነው

22ኛው አገር አቀፍ የኤች አይ ቪ ኤድስ በዓል “አሁንም ትኩረት ለኤችአይቪ መከላከል!” በሚል ቃል እየተከበረ መሆኑን የፌደራል የኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣሪያ ጽሕፈትቤት ገለጸ ፡፡

የጽሕፈትቤቱ የህዝብ ገንኙነት ኃላፊ አቶ ስንታዮህ ግርማ ለዋልታ እንደገለጹት፤ የአመራሩን ሚና በማጠናከር እና የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በኤችአይቪ እና ኤድስ ዙሪያ ያለዉን ግንዛቤና ዕዉቀት በማሳደግና የባህሪ ለዉጥ በማምጣት የሚጠበቅበትን ድርሻና ኃላፊነት እንዲወጣ ለማስቻል ዓላማ ያደረገ የዓለም የኤድስ ቀን እየተከበረ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

የዘንድሮውን የዓለም ኤድስ ቀን ልዩ የሚያደርገው የኤችአይቪ በየደረጃው ባለው አመራርና የሕብረተሰብ ክፍል የሚታየውን መዘናጋት በመስበር በፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ ዘርፈ ብዙ – ምላሽ የሚሰጥበት መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ሀገራችን ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች ለማስቀጠል የሚያስችል የመጨረሻ ምዕራፍ የንቅናቄ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለመተግበር የሚያስችል ሰነድ ዛሬ መጽደቁን ነው የተመለከተው ፡፡

ሰነዱም የአመራርና የህዝብ ፀረ – ኤችአይቪ /ኤድስ ንቅናቄ እየተካሄደ ባለበትና ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተፋጠነ  ምርመራና ህክምና ዘመቻ ለማካሄድ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል ፡፡

ይህንን ተግባር ለመፈጸም በፌዴራል ደረጃ ሥራዎቹን የሚመራና የሚከታተል ከባለድርሻ አካላት በተውጣጡ አባላት ዓብይ ኮሚቴና በሥሩ አስፈላጊ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል ነው ያሉት ፡፡

የክልሎች/የከተማ አስተዳደሮች የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤቶች/የጤና ቢሮዎች፣ የሴክተር መ/ቤቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ሲቪል ማህበራትና አጋር ድርጅቶች የዘንድሮው በዓል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር እንዲቻል የሚረጃ የመነሻ ሰነድ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል  ፡፡

ለዚሁም እ.ኤ.አ. በ2020 90 በመቶ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ተመርምረዉ የምርመራ ዉጤታቸዉን እንዲያዉቁ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

እንደዚሁም 90 በመቶ ተመርምው ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የተገኘ ወገኖችን የፀረ-የኤችአይቪ ሕክምና ይፈደረጋል ሲሉ አመልክተዋል ፡፡

በተጨማሪ 90 በመቶ የፀረ-የኤችአይቪ ሕክምና ውስጥ ያሉ ወገኖች በደማቸው ውስጥ የሚገኘውን የኤችአይቪ መጠን በሚፈለገው ደረጃ እንዲቀንስ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

አገራችን ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፋ በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል ፡፡

ለዚህ ተጋላጭነትን ትኩረት ያደረገ የኤችአይቪ ምርመራና ምክር አገልግሎት እና ጠንካራ የሆነ የትስስርና የቅብብሎሽ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡

ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸውን ወገኖች በአስቸኳይነት ስሜት የድጋፍና ክብካቤ እንዲሁም የፀረኤችአይቪ መድሃኒት እንዲያገኙ መደረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል ፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት መስጠት፤ ህክምናውን የጀመሩ እንዳያቋርጡና እና የሚያቋርጡ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት የሚያስችል ስልት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

ይሁን እንጂ በ2008 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ተመርምረው መድሃኒት መጀመር ከሚገባቸው ወገኖች መካከል 80 ሺህ የሚሆኑት አገልግሎት አልጀመሩም ነው ያሉት ፡፡   

ስለሆነም የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል የኤችአይቪ ምርመራ ዘመቻ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቀርጾ ወደ ትግበራ መገባቱን አስታውቀዋል ፡፡

በዓለም 78 ሚሊየን ሰዎች ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መያዛቸው ለማወቅ ተችሏል ፡፡