በመላ አገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ ዘርፉን የአፈጻጻም አቅም ይበልጥ ማጎልበት የሚያስችሉ የለውጥ መሣሪያዎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የፌደራል ተቋማት የሪፎርም ትግበራ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አጥሬ ለዋልታ እንደገለጹት በፌደራል ደረጃ የሲቪል ሰርቪሱን የማሻሻያ ፕሮግራም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚያስችሉ የአሠራር፣ የአደረጃጃትና የሰው ኃይል አቅም ማሳደጊያ መሣሪያዎች ትግበራ ላይ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ነው ።
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ የሲቪል ሰርቪሱ አገልግሎት አሠጣጥን በተሻለ ቅልጥፍናና ውጤታማነት በማከናወን የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ የለውጥ መሣሪያዎች ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ።
እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ሲደረጉ የቆዩት የለውጥ መሣሪያዎች የመሠረታዊ የለውጥ ሂደት ፣ የውጤት ተኮር ሥርዓት፣ የዜጎች ቻርተርና የለውጥ ሠራዊት መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛው ቁርጠኛ የህዝብ አገልጋይነት ባህሪን እንዲላበስ እገዛ እያደረጉ ናቸው ።
የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃይል ልማት ሚኒስቴር በመላ አገሪቱ የሚገኙት የሲቪል ሰርቪስ መዋቅሮች የለውጥ ማሻሻያ ፕሮግራሙን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የመደገፍና መከታተል ሥራን እንደሚያከናውን የገለጹት አቶ ተስፋዬ የለውጥ ሥራው እውን እንዲሆን አስፈላጊው የቴክኒክ፣ የሥልጠናና የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል ።
ተቋማት የመልካም አስተዳደር አካል የሆነውን የለውጥ ተግበራ የአፈጻጻም ደረጃ በየወሩ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚልክበት አሠራር መዘርጋቱን የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ የእያንዳንዱ ተቋም የለውጥ ሂደት በየሩብ ዓመቱ በሚንስትር ደረጃ እየተገመገመ እንደሚገኝ አስረድተዋል ።
በመላ አገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ የለውጥ መሣሪያዎችን ይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛውና አመራሩ በልዩ ትኩረት እንዲሠሩ አቶ ተስፋዬ ጥሪ አቅርበዋል ።