በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለዶክተር አብይ አህመድ የለውጥ ስራዎች የድጋፍ ሰልፍ አደረጉ

በአሜሪካ ዋሸንግተን፣ በሲያትል እና አካባቢ ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የዶክተር አብይ አህመድን የለውጥ ስራዎች በመደገፍ ሰልፍ አደረጉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዛሬ  ጀምሮ ለሶሰት ቀናት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስና ሚኒሶታ ከተሞች በመገኘት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ዳያስፖራ ማህበረሰብ ጋር ይወያያሉ፡፡

ከውይይቱ በፊትም በዋሸንግተን ዲሲ፣ በሲያትል ከተሞችና አካባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸውን የለወጥ ስራዎች በመደገፍ ሰልፍ አካሂደዋል።

በሲያትል ከተማ በሚገኘው በታላቁ የነጻነት መሪ በሆኑት በማርቲን ሉተር ኪንግ ስም በተሰየመው “ኪንግስ ሆል” ፊት ለፊት በተደረገው ሰልፍ ላይ፣ የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር እርምጃዎች የሚደግፉ እና ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚሰብኩ መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡

ለዓመታት የኢትዮጵያን መንግሥት በሚቃወሙም ሆነ የሚደግፉ ኢትዮጵያዊያን፣ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራውያንን ጨምሮ ታዋቂ የፖለቲካ እና የኪነጥበብ ሰዎች በሰልፉ ላይ ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሐምሌ 22 ቀን 2010   “የጥላቻና የልዩነት ግንብን አፍርሰን የፍቅርና የአንድነት ድልድይ እንገነባለን” በሚል መሪ ሀሳብ በዋልተር ኢ ዋሽንግተን የስብስባ ማዕከል ከኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ይወያያሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ በሚኖራቸው ቆይታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው እየተካሄደ ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ አካል ሆነው ለአገሪቱ ልማትና እድገት አስተዋጽኦ በሚያደርጉበት ሁኔታ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉዞ የመንግስት ለመንግስት ግንኙነትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን  ማህበረሰብ ጋር መወያየትን ዋና ዓላማ ያደረገ እንደሆነ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን ከተለያዩ አካላት የተወጣጣ  የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ኢምባሲው አስታውቋል። (ኢዜአ)