ፖሊስ የኢንጂነር ስመኘው በቀለን አሟሟት የምርመራ ውጤት ይፋ እስኪያደርግ ሁሉም ዜጋ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ

ፖሊስ በኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሟሟት ላይ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እስኪያደርግ ሁሉም ዜጋ በትዕግስት እንዲጠብቅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን  ጥሪ አቀረቡ።

አቶ ደመቀ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ እና የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለቱን ኢትዮጵያዊያን ሞት አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለኢንጂነር ስመኘው በቀለ፣ ለአቶ ተስፋዬ ጌታቸው ቤተሰቦች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያዊ መጽናናትን ተመኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በኢትዮጵያ የሃይል ልማት ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋንያን ነበሩ።

“የኢንጂነር ስመኘው አሟሟት ልብ ሰባሪ ነበር” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ፖሊስ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እስኪያደርግ ሁሉም ዜጋ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢንጅነር ስመኘውን ለመካስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን እንዲሆን ከመቸውም ጊዜ በላይ መረባረብ እንዳለበትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ፖሊስ ተገቢውን ማጣራት አጠናቆ ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እስኪያደርግ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የጠቆሙት አቶ ደመቀ፤ ህዝቡም ከፖሊስ ጎን በመቆም ተገቢ ትብብር ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ አያይዘውም የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

አቶ ተስፋዬ ለዴሞክራሲ እና የህግ የበላይነት መስፈን ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ ዋጋ የከፈሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ እንደነበሩም አስታውሰዋል።

አቶ ተስፋዬ እጅግ ሲበዛ የመርህ ሰው እንደነበሩ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሁላችንም ለፍትህና የህግ የበላይነት መስፈን የበኩላችንን በመወጣት የእርሳቸውን ፈለግ መከተል አለብን” ሲሉም ተናግረዋል። (ኢዜአ)