እጅግ ወሳኝ በሆነ የእጣ ፈንታችንን አቅጣጫ አመላካች ጊዜ ላይ እንገኛለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

በሃገራችን ታሪክ ውስጥ እጅግ ወሳኝ በሆነ የእጣ ፈንታችንን አቅጣጫ አመላካች ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  አህመድ በሚኒሶታ ለኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተናግረዋል፡፡

ግድቡን አፍርሰን ድልድዩን እንገንባ የሚል መሪ ሃሳብ የያዘውና  በዶክተር አቢይ የተመራው የልዑካን ቡድን ከዋሽንግተን ዲሲ እና ላስቬጋስ በኋላ ወደ ሚኒሶታ በመሄድ ከኢትዮጵያዊያን  ጋር  ውይይት አድርጓል፡፡

ዶክተር አብይ በመንትዮቹ የሚኒያፖሊስ እና ሴንትፖል ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉልን አቀባበል በፍቅር እንድንማረክና በፍቅር እንድናገለግል ያደርገናል ብለዋል፡፡

የጉዟችን መሪ ሃሳብ ግድቡን አፍርሰን ድልድዩን እንገንባ የሚል ቢሆንም ግድቡ በዋሽንግተን እና በሎስ አንጀለስ ፈርሷልና ለሚኒሶታ ያለኝ ግብዣ ፍርስራሹን በጋራ እናጽዳ የሚል ነውም ብለዋል፡፡

አንዲት ታላቅ ሃገር በጋራ  ለመገንባት የቆማችሁ ህዝቦች በዚህ ስፍራ ስላላችሁ በኢትዮጵያ ህዝብና በቲም ለማ ስም ያለኝን ምስጋናና አድናቆት እገልጻለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

መሪ ቃላችን እንደሚጠቁመው ዛሬ በየሃገሩ የተበተነው ህዝባችን ከሃገሩና ከወጣበት ማህበረሰብ ጋር ተደምሮ በሃገሩ ላይ እንዳይወሰን እና እንዳይሳተፍ ለአመታት የተጋረጠበትን የመለያየት ግንብ መጋፈጥና መደርመስ ይኖርበታል፡፡

በመላው አሜሪካ እና በውጭ በሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ መካከል ይህ ግንብ ተጋርጦ ሁሉም በየጎራውና በየቡድኑ የጎሪጥ እንዲተያይና አንዱ የሌላው ስጋት እንዲሆን አድርጎ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና አቶ ለማ እንዳሉት አማራ ለኦሮሞ፤ ኦሮሞ ለሱማሌ፤ ሱማሌ ለጋምቤላው፤ ጋምቤላው ለወላይታው ስጋት ሳይሆን ኩራቱ ነው ብለዋል፡፡

እዚህ ያላችሁ ጎልማሶችና ሽማግሌዎች ህጻናት ከነዚህ ባህሎች አንዱን ቢዘነጉ ሃላፊነት መውሰድ የሚገባን እኛ እንጂ እነሱ አይደሉም፤ ምክንያቱም ላለፉት አመታት ያላስተማርናቸውን ከዬት ያመጡታል ብለዋል፡፡

ልጆቻችን ተነጋግረው መግባባት ተቀራርበው መወያየት ወደማይችሉበት የጠላትነት ደረጃ ላይ አድርሰናቸው ስለቆየን ሃላፊነቱን መውሰድ ብቻ ሳይሆን ያ ለማካካስ ቀን ከለሊት ተደምረን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡