ሰራዊቱን በማጠናከር አንድነትና የህግ የበላይነትን ማስፈን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

የመከላከያ ሰራዊትን በዘመናዊ መንገድ በማጠናከር አንድነትና የህግ የበላይነትን ማስፈን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለተኛ ዲግሪ እና በዲፕሎማ የሰለጠኑ የአገር መከላከያ መኮንኖችን የመረቁ ሲሆን መከላከያው በህገ-መንግስቱ በመመራት ከማንኛውም ፖለቲካና መሰል ግፊቶች ነፃ በመሆን ህዝባዊውን ለውጥ እንዲያስቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የህግ ጥሰት እንቅስቃሴዎች መቆም እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት ።

ነፃነትና ስርዓት አልበኝነትን ባለመለየት መረን የወጣ፣ህግና ስረአትን የማያከብር፣ የመንጋ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ መቆም ይኖርበታል።ህጋዊ ስረአት እያዳከምን በመንግስት የሚሰጥ ፍትህ ተከትለን የፍትህ ስረአቱን በግል ስሜት የምንነዳው ከሆነ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ያልተጠናከረው ስረአት ያልተጠናከረው ሃገር ወደማይወጣው ስረአት የሚያስገባና ሁሉንም በኪሳራ የሚያስጨርስ በመሆኑ የህግ ልዕልናን ጠንቅቆ ማወቅና ማክበር ማስከበር የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ሲሆን የአገር መከላከያ ሰራዊት ደግሞ ድርብ ሃላፊነት ይኖረዋል። ህግ አልባና አመፅን የሚታገስ ስረአት እንደሃገር መቆጠራችንን ከንቱ ስለሚያደርግ አገራዊ አንድነታችንን በህግ አግባብ ማስጠበቅ የዘወትር ተልዕኮአችን ይሆናል

መንግስት የአገር መከላከያ ተቋም ከወቅታዊ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማገዝና የማጠናከሪያ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀው ተመራቂዎቹም ዕውቀታቸውን ለሌሎች በማካፈል ይህንኑ ስራ እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

የወታደራዊ ጥበብ መለኪያ የሆነውን አንዱ ፕሮፌሽናል ተቋም መገንባት ነው ስለሆነም ዛሬ የተመረቃችሁ ላለፉት አመታት ሳይንስን ጥበብን ያጠናችሁ የተመራመራችሁ ወደሃላፊነታችሁ ስትመለሱ ይህንን እውቀት ለብዙዎች በማካፈል ፕሮፌሽናል አርሚ ለመገንባት ከነገ ጀምሮ በታላቅ ትጋት ስራችሁን እንድትጀምሩ በዚህ አጋጣሚ አደራ ለማለት እፈልጋለሁ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንንና ሰራዊቱ በኢትዮጵያ ምስራቅና ምዕራብ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት ከማረጋጋትና ህግና ስርአት እንዲከበር የሰሩትን ውጤታማ ስራ አድንቀዋል።

ህግና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ቢሆንም የመከላከያ ሰራዊት ድርብ ኃላፊነት መሆኑንና አሁን እየታየ ያለው ህዝባዊ ለውጥ በስርዓት አልበኝነትና በህግ ጥሰት እንዳይቀለበስ መከላከያው እየተወጣ ያለው ግዴታ የሚበረታታና መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።

እያንዳንዱ ወታደርና የጦር መኮንን ጀግና መሆን አለበት ሲባል ተኩሶ መግደል ብቻ ሳይሆን ስሜቱን የሚያሸንፍ ህገ መንግስቱን የሚያውቅ ለዚያ የሚገዛ ቁርጠኛ መሆኑን በየእለቱ የሚያረጋግጥ መሆን ይጠበቅበታል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን በበኩላቸው የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል የሚያስችል የመከላከያ ሰራዊት እየተገነባ መሆኑንና ይህም እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የተጀመረው ሃገራዊና ተቋማዊ ሪፎርም ለማስቀጠል እንዲቻል ትምህርትና ስልጠና ላይ ስራ የሚያስፈልገን መሆኑን አይተናል ይህን አይነት ሰው ለመፍጠር ትምህርትና ስልጠና ወሳኝ ነው በመሆኑም የኢፌድሪ መከላከያ ይህን ተገንዝቦ በመጭው አዲስ አመት መጀመሪያ ከመከላከያና ከሌሎች መንግስታዊ የፀጥታ ተቋማት የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮችን ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገበት ያለውን ኮሌጅ ጨምሮ ባለፉት አመታት የሙያ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጡ ተቋሞችን በማቋቋም አስተምሮና አሰልጥኖ ወደስራ እንዲሰማሩ አድርጓል።

በዛሬው ዕለት የተመረቁት መኮንኖች 130 ሲሆኑ 10ሩ የውጭ አገር ዜጎች ናቸው።

ከተመራቂዎቹ የሰራዊቱ አባላት መካከል በከፍተኛ ውጤት በወርቅ ማዕረግ የተመረቁት አምስቱ ልምድ ለመቅሰም በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ውጭ የጉብኝት ፕሮግራም እንደሚኖራቸው ተገልጿል። (ኢዜአ)