የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ኮፊ አናን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ጋናዊው ኮፊ አናን በ80 ዓመታቸው ስዊዘርላንድ ጀኔቫ ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

በሰብዓዊ ድጋፍ ስራቸው የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ኮፊ አናን ከማረፋቸው በፊት ትንሽ ህመም ተሰምቷቸው እንደነበር በስማቸው የተቋቋመው ፋውንዴሽን ገልጿል።

አናን ከፈረንጆቹ 1997 እስከ 2006 ድረስ  የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ተቋሙን በመምራትም የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ናቸው።

ከዋና ጸሃፊነታቸው ቀጥሎ በተባበሩት መንግስታት የሶሪያ ቀውስ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ሰርተዋል።

የኮፊ አናን ፋውንዴሽን ባወጣው የሀዘን መግለጫ፥ በህይወት ዘመናቸው ለዓለም ፍትሃዊነትና ሰላማዊነት በትጋት ሲሰሩ ነበር ብሏል።

በፈረንጆቹ 2001 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተሻለ ስራ እንዲያከናውን ባደረጉት ጥረት የሰላም ኖቤል ተሸልመዋል።

ኮፊ አናን ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚጠቀስባቸው ስራዎች መካከል እንደ ድህነት ቅነሳ እና የህጻናት ሞት ማስቀረትን ጨምሮ “የሚሊኒየሙ ዘላቂ የልማት ግቦች” የሚሉት ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ይጠቀሳሉ።

(ምንጭ፦ቢቢሲ)