የኢትዮጵያ መንግስትና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር /ኦብነግ/ በአስመራ ውይይት አደረጉ

የኢትዮጵያ መንግስትና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር /ኦብነግ/ በአስመራ ውይይት አደረጉ፡፡

በኢፌዴሪ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የሚመራ ልዑክ ነው ወደ አስመራ በማቅናት ከኦብነግ ጋር ውይይት ያካሄደው፡፡

በኦብነግ በኩል ደግሞ ሊቀመንበሩ ሞሃመድ ኦማር ናቸው በውይይቱን የተገኙት ተብሏል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በግንባሩ ቃል አቀባይ አቶ አዳኒ አብዱልቃድር ሄርሞጌ የተመራው እና 3 አባላትን ያለው ልኡክ አዲስ አበባ መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡

ወደ ሀገር ቤት መግባቱ ተከትሎም ልዑኩ የተናጠል የተኩስ አቁሙ ተፈፃሚ እንደሚያደረግም መግለጹ ይታወቃል፡፡

በወቅቱ ኦብነግ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ የደረሰውም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ እንደሆነም ግንባሩ በመግለጫው ማንሳቱ ይታወሳል።

በኦጋዴን ያለውን ግጭት በውይይት እና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት ከኢትዮጵያ መንግስት የጀመራቸውን መልካም እርምጃዎች እንደሚቀበልም ኦብነግ ገልጸ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትና ኦብነግ ትናንት ያደረጉት ውይይትም ይህንን መሰረት በማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ የሚገኙ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ገብተው በፖለቲካው ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት አርበኞች ግንቦት 7 እና ኦነግን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፡፡

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 28 2010 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባው የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) የሽብርተኝነት ፍረጃ ማንሳቱ ይታወሳል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2003 ዓ.ም ነበር ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት 7 እንዲሁም ከሀገር ውጪ አልቃይዳና አልሸባብን ጨምሮ አሸባሪ ድርጅቶች ብሎ የፈረጀው።(ኤፍ.ቢ.ሲ)