ሚኒስቴሩ በሚሲዮኖች አገልግሎት ዘርፍ የሚሠሩ ከ90 በላይ ሠራተኞችን ወደ አገር ቤት መጥራቱን አስታወቀ

 ለረዥም ዓመታት በተለያዩ የውጭ አገራት ኢትዮጵያን  በመወከል በሚስዮኖች በአገልግሎት ዘርፍ ሲሰሩ የነበሩ ከ90 በላይ ሰራተኞችን ወደ አገር ቤት መጥራቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚጠበቁት እነዚህ ሰራተኞች ከ4 አስከ 25 ዓመታት በኤምባሲዎች እና በቆንስላ ጽህፈት ቤቶች የቆዩ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ 130 ዲፕሎማቶች አስፋላጊውን ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ሀገራቸውን በተለያዩ ኃላፊነቶች እንዲያገለግሉ ወደ ኤምባሲዎች መመደባቸውም ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጥንቶ ያቀረበው መዋቅር በፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር ከታየ በኋላ በጠቅላይ ሚንስትሩ በመጽደቁ በቅርቡ የዲፕሎማቶች ዳግም ምደባ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።

በዚህም መሠረት በመስሪያ ቤቱ የሰው ሃይል ምደባ መስፈርት መሰረት በሁሉም ሚሲዮኖች የሚገኙ ዲፕሎማቶች ዳግም ምድባ የሚያካሂድ ሲሆን፥ ይህም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የሙያ ክህሎት ያጠናክራል ተብሎ ታምኖበታል።( ምንጭ: የውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽህፈትቤት)