11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ዶክተር አብይ አህመድን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ፣ አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ ።
በሐዋሳ ከተማ ለሦስተኛ ቀን እየተካሄደ ባለው የ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ የድርጅቱን የሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ለመምረጥ ድምጽ የመሥጠት ሥነ -ሥርዓት ተካሄዶ ዶክተር አብይ አህመድና አቶ ደመቀ መኮንን በሊቀመንበርነትና በምክትል ሊቀመንበርነት በድጋሚ ተመርጠዋል ።
ኢህአዴግ በዛሬው ዕለት ባካሄደው የአመራር ምርጫ ዶክተር አብይ አህመድ፣ አቶ ደመቀ መኮንንና ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን በእጩነት ያቀረበ ሲሆን ሶስቱም ለኢህአዴግ ለሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበርነት ተወዳድረዋል ።
የድርጅቱን መሪዎች ለመምረጥ በአጠቃላይ 177 ሰዎች ድምጽ እንዲሠጡ የተደረገ ሲሆን ዶክተር አብይ አህመድ 176 ድምጽ በማግኘት ነው ለቀጣይ ዓመታት የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው እንዲያገለግሉ የተመረጡት ።
ለኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነት በተሠጠው ድምጽ አቶ ደመቀ መኮንን አጠቃላይ ከተሠጠው ድምጽ የ149 ሰዎች ድምጽን በማግኘት ነው የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ።
ሌላው ተወዳዳሪ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ለድርጅቱ አመራርነት በተሠጠው በአጠቃላይ 15 ድምጽ አግኝተዋል ።