ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጀርመን የሚያደርጉትን ጉብኝት ጀምረዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አውሮፓ ጉብኝታቸውን ከፈረንሳይ በመቀጠል ጀርመን በርሊን ገብተዋል።

የጀርመን መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክልም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ረፋድ ላይ ነው በርሊን የገቡት፡፡

በርሊን ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ሲደርሱም በጀርመን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኩማ ደመቅሳና የጀርመን መንግስት ተወካዮችና ዲፕሎማቶች አቀባበል አደርገውላቸዋል።

በጀርመን ቆይቸውም ከቻንስለር አንሄላ ሜርክል ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተበሎ እየተጠበቀ ነው።

ውይይቱ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብርን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

ከቻንስለር አንጌላ ሜርክል ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በበርሊን በሚከፈተውና ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ድጋፍ በማደረግ ላይ የሚያተኩረው ቡድን ሃያ ሃገራት ኢኒሼቲቭ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ።

ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2017 በጀርመን አነሳሽት የተጀመረ ነው።

ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ መሰረተ ልማትን ጨምሮ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማጠናከርና ለማበረታት የተጀመረ ኢኒሼቲቭ ነው።

የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚና የፋይናንስ መዋቅራቸውን ሳቢ በማድረግ የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንት በስፋት እንዲሰማራ የሚደግፍ መርሃ ግብር ነው።

በዚህም በሀገራቱ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በስፋት ያስተዋውቃል።

በሀገራቱ የሚወሰዱ የማሻሻያ አጀንዳዎችና የፖሊሲ እርምጃዎችንም ይደግፋል።

ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ የቡድን ሃያ አባል ሀገራትን፣ ለለውጥ ዝግጁ ናቸው፣ የለውጥ አሥተሳሰብን ያራምዳሉ የሚባሉ አፍሪካ ሀገራትንና ዓለም ዓቀፍ አጋሮችን ያሰባሰበ ነው።

እስካሁንም ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ግብጽ፣ ጋና፣ ሴኔጋልና ሞሮኮን ጨምሮ አስራ አንድ የአፍሪካ ሀገራት በዚህ ኢንሼቲቭ ተካተዋል።

በዛሬው ስብሰባ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትና መንግስታት መሪዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)