በደቡብ ሱዳን ህፃናት ያለዕድሚያቸው እንዲያገቡ የሚደረጉበትን ሁኔታ የሀገሪቱ መንግስት እንዲያስቆም ተጠየቀ

በደቡብ ሱዳን ህፃናት ያለዕድሚያቸው አየተገደዱ እንዲያገቡ የሚደረጉበትን ሁኔታ የደቡብ ሱዳን መንግስት እንዲያስቆም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጠየቁ፡፡

በደቡብ ሱዳን ሴት ህፃናት በለጋ እድሚያቸው ከትምህርት እያቋረጡ እንዲያገቡ እየተደረገ እና በጁባ የማይታወቅ ቦታ እየተወሰዱ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በደቡብ ሱዳን በህፃናት ላይ ሚደርሰው ይህንን አሰቃቂ እና ህገ ወጥ ተግባርም እልባት እንዲበጅለት ነው በሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የመብት ተከራካሪ ድርጅቶች ያስታወቁት፡፡

በደቡብ ሱዳን በአሁኑ ሰዓት ከ52 በመቶ በላይ የሚሆኑ ከ18 አመት በታች የሆኑ ሴት ህፃናት እየተገደዱ እና ትምህርታቸውን እያቋረጡ እንዲያገቡ እንደተደረጉ ተጠቅሷል፡፡

በደቡብ ሱዳን ህፃናት ትምህርታቸውን እያቋረጡ እንዲያገቡ የሚደረግበት ምክንያት በዋናነት በሀገሪቱ በተንሰራፋው ድህነት ሲሆን ድህነትን ለመቋቋም ሲሉ ሴት ህፃናት ያለ እድሚያቸው  መስዋዕት እየሆኑም ነው ተብሏል፡፡  

በደቡብ ሱዳን አሁን ላይ በአማካኝ ከ10 ሴት ህፃናት አንዷ ብቻ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የምትሳተፍ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በእናቶችና ህፃናት ሞት ከአለማችን ቁጥር አንድ የሆነችው ደቡብ ሱዳን አንድ በመቶ የሚሆኑ ህፃናት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚደርሱ መሆኑም የተጠቆመ ሲሆን ሌሎች ለእድሚያቸው እየተገደዱ ወደ ጋብቻ የሚገቡ ናቸው፡፡

ከአለም ሀገራት ትንሽ እድሜ ባላት ደቡብ ሱዳን ህፃናትን ያለ እድሚያቸው ለጋብቻ ማቅረብ ህፃናትን ካልተፈለገ እርግዝና እና ትንኮሳ ይከላከላል ተብሎ ይታመናል፡፡

በደቡብ ሱዳን ጠንካራ የጋብቻ ህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በርካታ የደቡብ ሱዳን ማህበረሰቦች ሴት ህፃናት ልጆቻቸውን ለጋብቻ የሚያቀርቡት  በተለያዩ ስጦታዎችን ማለትም በግመል እና ሌሎች እንስሳት ስጦታ ነው፡፡

ይህንን ተከትሎ ህፃናት ለተለያዩ በሽታዎች በመጋለጥ ለሞት እየተዳረጉም ይገኛሉ፡፡ የመብት ተከራካሪዎችም የደቡብ ሱዳን መንግስት በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲያስቆምም ነው የጠየቁት፡፡ (ምንጭ፡-ሱዳን ትሪቡዩን)