ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዜጎች የትምህርት ዕድል ሰጠች

ኢትዮጵያ 306 ለሚሆኑ የሶማሊላንድ ዜጎች በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ደረጃዎች የትምህርት ዕድል መስጠቷን ተገለጸ፡፡

ዕድሉ ከተሰጣቸው 200 ያህሉ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 100 በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም 6 በዶክትሬት ዲግሪ እንደሆነና  እድሉ ከተሰጣቸው ተማሪዎች 60 ያህሉ ሴቶች እንደሆኑ ታውቋል፡፡

የእንኳን ደህና መጣችሁና የአቀባበል ፕሮግራም ላይ በኢትዮጵያ የሶማሊላንድ አምባሳደር አሕመድ ኤጋል እደተናገሩት ኢትዮጵያ የትምህርት ዕድሉን ለሶማሊላንድ ተማሪዎች መስጠቷ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የትምህርትና ባሕል ግንኙነት ወደላቀ የትብብር ምዕራፍ ለማሸጋጋርና ያግዛል፡፡ የሶማሊላንድ መንግስት ኢትዮጵያ ላበረከተችው አስተዋፅኦ ምስጋና እንደሚያቀርብና በቀጣይም የሁለቱን አገራት የትብብር መስኮች ለማጎልበት እንደሚሰራ አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ዕድሉን ካገኙት ተማሪዎች መካከል ማህዲ አስማኤል በበኩሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ለመማር እንደተመደበና ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ፀጥታን ለማጎልበት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የእውቀቱን ለማበርከት እንደሚተጋ ተናግሯል፡፡

በዕለቱ የሶማሊላንድ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሰመረ እንዲሆን አቅጣጫሰጥተዋል፤ ምክርም ለግሰዋል፡፡

ተማሪዎች በአዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ ወሎ፣ አምቦ፣ ወልቂጤ፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ፣ ሐሮማያ፣ ባህርዳር እና አርባምንጭ በሚገኙ የመንግስት የኒቨርሲቲዎች እንደተመደቡና ወደ ዩኒቨርሲቲዎቹም እየገቡ እንደሆነ ታውቋል፡፡