የሰላም ኮንፈረንስ በድሬደዋ እየተካሄደ ነው

አራት የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልሎችና አንድ ከተማ አስተዳደርን ያሳተፈ የሰላም ኮንፈረንስ በድሬደዋ እየተካሄደ ነው።

መድረኩን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው ከኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ሀረሪ ክልሎች  እና ድሬ ደዋ ከተማ  ጋር በመተባበር ”ብዘሃነት፣ መቻቻልና እርቅ ለአገር አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በሰላም ዙሪያ በጋራ ለመምከር ያዘጋጀው።

ዛሬ ና ነገ በሚካሄደው በዚህ መድረክ ከእነዚህ ክልሎች የተወጣጡ 500 የሚሆኑ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የምክር ቤት አፈጉባዔን ጨምሮ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የግጭት አፈታት፣ የሰላም እሴት ግንባታ ጥናትና ንቃተ ህግ መንግስት ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ተክሌ እንዳሉት መድረኩ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶት መበራከታቸው ጋር ተያይዞ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

የሚከሰቱ ግጭቶች በአገሪቱ ህዝቦች መካከል የነበሩ የአብሮነት እሴትን እየሸረሸሩ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ይህም በቅርቡ የሚከበረው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ጨምሮ መሰል መድረኮች በተለያዩ አከባቢዎች ሲዘጋጁ ስለ ሰላም እየተመከረ መሆን ይገባል ብለዋል።

በዛሬው እለት በምስራቅ ኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር የተጀመረውም ኮንፍረንስ የዚሁ አካል ሲሆን በመድረኩ መጨረሻም የግጭት አስከፊነት፣ አገራዊ አንድነት፣ እርቅና የመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ይፈጠራል ተብሎ ይታሰባልም ብለዋል።

በድሬደዋ የተጀመረው መድረክ እስከ ህዳር 29 ማለትም የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ቀን ክብረ በዓል ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄድ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት በምዕራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝን፣ ኦሮሚያና አማራን ያሳተፈ መድረክ በአሶሳ ይካሄዳል ተብሏል።(ኢዜአ)